← Zechariah (13/14) → |
1. | በዚያ ቀን ለዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ከኃጢአትና ከርኵሰት የሚያነጻ ምንጭ ይከፈታል። |
2. | በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የጣዖታትን ስም ከምድር አጠፋለሁ፥ ከዚያም በኋላ አይታሰቡም፤ ደግሞም ሐሰተኞችን ነቢያትና ርኩስ መንፈስን ከምድር ላይ አስወግዳለሁ። |
3. | ማንም ደግሞ ትንቢት ቢናገር የወለዱት አባቱና እናቱ። አንተ በእግዚአብሔር ስም ሐሰትን ተናግረሃልና በሕይወት አትኖርም ይሉታል፤ ትንቢትንም ሲናገር የወለዱት አባቱና እናቱ ይወጉታል። |
4. | በዚያም ቀን ነቢያቱ ሁሉ ትንቢትን ሲናገሩ እያንዳንዱ ስለ ራእዩ ያፍራል፤ ያታልሉም ዘንድ የማቅ ልብስ አይለብሱም። |
5. | እርሱ ግን። ከታናሽነቴ ጀምሮ ባሪያ ሆኜ ነበርሁና ገበሬ ሰው ነኝ እንጂ ነቢይ አይደለሁም ይላል። |
6. | ሰውም። ይህ በእጅህ መካከል ያለ ቍስል ምንድር ነው? ይለዋል። እርሱም። በወዳጆቼ ቤት የቈሰልሁት ቍስል ነው ይላል። |
7. | ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ፤ እጄንም በታናናሾች ላይ እመልሳለሁ። |
8. | በምድርም ሁሉ ላይ ሁለት ክፍል ተቈርጠው ይሞታሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሦስተኛውም ክፍል በእርስዋ ውስጥ ይቀራል። |
9. | ሦስተኛውንም ክፍል ወደ እሳት አገባለሁ፥ ብርም እንደሚነጥር አነጥራቸዋለሁ፥ ወርቅም እንደሚፈተን እፈትናቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜን ይጠራሉ፥ እኔም እሰማቸዋለሁ፤ እኔም። ይህ ሕዝቤ ነው እላለሁ፤ እርሱም። እግዚአብሔር አምላኬ ነው ይላል። |
← Zechariah (13/14) → |