Zechariah (1/14) → |
1. | በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ። |
2. | እግዚአብሔር በአባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቈጥቶ ነበር። |
3. | ስለዚህ እንዲህ በላቸው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ እኔ ተመለሱ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። |
4. | የቀደሙት ነቢያት ለአባቶቻችሁ እንዲህ ብለው ሰብከዋል። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ፤ እነርሱ ግን አልሰሙም፥ እኔንም አላደመጡም፤ እንደ እነርሱ አትሁኑ፥ ይላል እግዚአብሔር። |
5. | አባቶቻችሁ ወዴት ናቸው? ነቢያትስ ለዘላለም በሕይወት ይኖራሉን? |
6. | ለባሪያዎቼስ ለነቢያት ያዘዝኋቸው ቃሎቼና ሥርዓቴ በአባቶቻችሁ ላይ አልደረሱምን? እነርሱም ተመልሰው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በመንገዳችንና በሥራችን መጠን ያደርግብን ዘንድ እንዳሰበ እንዲሁ አድርጎብናል አሉ። |
7. | በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመት ሳባጥ በሚባል በአሥራ አንደኛው ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ። |
8. | እነሆም፥ አንድ ሰው በመጋላ ፈረስ ተቀምጦ በሌሊት አየሁ፥ እርሱም በሸለቆው ውስጥ ባሉ በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ነበር፤ በስተ ኋላውም መጋላና ሐመር አንባላይም ፈረሶች ነበሩ። |
9. | እኔም። ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁ። ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ። እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አሳይሃለሁ አለኝ። |
10. | በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ የነበረው ሰው። እነዚህ በምድር ላይ ይመላለሱ ዘንድ እግዚአብሔር የላካቸው ናቸው ብሎ መለሰ። |
11. | በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ የነበረውን የእግዚአብሔርን መልአክ። በምድር ላይ ተመላለስን፥ እነሆም፥ ምድር ሁሉ ዝም ብላ ዐርፋ ተቀምጣለች ብለው መለሱለት። |
12. | የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ። አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ። |
13. | እግዚአብሔርም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው። |
14. | ስለዚህም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ። ስበክ እንዲህም በል። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ በታላቅ ቅንዓት በኢየሩሳሌምና በጽዮን ቀንቻለሁ። |
15. | እኔ ጥቂት ብቻ ተቈጥቼ ሳለሁ እነርሱ ክፋትን ስላገዙት፥ ባልተቸገሩት አሕዛብ ላይ እጅግ ተቈጥቻለሁ። |
16. | ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ፤ ቤቴ ይሠራባታል፤ በኢየሩሳሌምም ላይ ገመድ ይዘረጋበታል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። |
17. | ደግሞም እንዲህ ስትል ስበክ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከተሞቼ ደግሞ በበጎ ነገር ይረካሉ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ ጽዮንን ያጽናናል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ይመርጣል። |
18. | ዓይኖቼንም አንሥቼ እነሆ፥ አራት ቀንዶች አየሁ። |
19. | ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረውን መልአክ። እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት። እርሱም። እነዚህ ይሁዳንና እስራኤልን ኢየሩሳሌምንም የበተኑ ቀንዶች ናቸው ብሎ መለሰልኝ። |
20. | እግዚአብሔርም አራት ጠራቢዎች አሳየኝ። |
21. | እኔም። እነዚህ የመጡት ምን ሊሠሩ ነው? አልሁ። እርሱም። አንድ ሰው ራሱን እስከማያነሣ ድረስ እነዚህ ቀንዶች ይሁዳን የበተኑ ናቸው፤ እነዚህ ግን ሊያስፈራሩአቸው፥ የይሁዳንም አገር ይበትኑ ዘንድ ቀንዳቸውን ያነሡትን የአሕዛብን ቀንዶች ሊጥሉ መጥተዋል ብሎ ተናገረ። |
Zechariah (1/14) → |