← SongOfSongs (7/8) → |
1. | አንቺ ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ፤ እናይሽ ዘንድ ተመለሽ፥ ተመለሽ። በሱላማጢስ ምን ታያላችሁ? እርስዋ እንደ መሃናይም ዘፈን ናት። |
2. | አንቺ የመኰንን ልጅ ሆይ፥ እግሮችሽ በጫማ ውስጥ እንዴት ውቦች ናቸው! ዳሌዎችሽስ በአንጥረኛ እጅ እንደ ተሠሩ እንደ ዕንቍዎች ይመስላሉ። |
3. | እንብርትሽ የወይን ጠጅ እንደማይጐድልበት እንደ ተነጠጠ ጽዋ ነው፤ ሆድሽ እንደ ስንዴ ክምር፥ በአበባም እንደ ታጠረ ነው። |
4. | ሁለቱ ጡቶችሽ እንደ ሁለቱ መንታ እንደ ሚዳቋ ግለገሎች ናቸው። |
5. | አንገትሽ እንደ ዝሆን ጥርስ ግንብ ነው፤ ዓይኖችሽ በሐሴቦን ውስጥ በባትረቢ በር አጠገብ እንደ ውኃ ኵሬዎች ናቸው፤ አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አፋዛዥ እንደሚመለከት እንደ ሊባኖስ ግንብ ነው። |
6. | ራስሽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ በላይሽ ነው፤ የራስሽም ጠጕር እንደ ሐምራዊ ሐር ነው፤ ንጉሡ በሹርባው ታስሮአል። |
7. | ወዳጄ ሆይ፥ እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ደስ ታሰኛለሽ! |
8. | ይህ ቁመትሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፥ ጡቶችሽም የወይን ዘለላ ይመስላሉ። |
9. | ወደ ዘንባባው ዛፍ እወጣለሁ ጫፎችዋንም እይዛለሁ አልሁ፤ ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ የአፍንጫሽም ሽቱ እንደ እንኮይ ናቸው። |
10. | ጕሮሮሽ ለወዳጄ እየጣፈጠ እንደሚገባ፥ የተኙትን ከንፈሮች ይናገሩ ዘንድ እንደሚያደርግ፥ እንደ ማለፊያ የወይን ጠጅ ነው። |
11. | እኔ የውዴ ነኝ፥ የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው። |
12. | ውዴ ሆይ፥ ና፥ ወደ መስክ እንውጣ በመንደሮችም እንደር። |
13. | ወደ ወይኑ ቦታ ማልደን እንሂድ፤ ወይኑ አብቦ አበባውም ፍሬ አንዠርግጎ ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እንይ፤ በዚያ ውዴን እሰጥሃለሁ። |
← SongOfSongs (7/8) → |