← SongOfSongs (5/8) → |
1. | እኅቴ ሙሽራዬ ሆይ፥ ወደ ገነቴ ገባሁ፥ ከርቤዬን ከሽቱዬ ጋር ለቀምሁ፥ እንጀራዬን ከማሬ ጋር በላሁ፥ የወይን ጠጄን ከወተቴ ጋር ጠጣሁ። ባልንጀሮቼ ሆይ፥ ብሉ፤ ወዳጄ ሆይ፥ ጠጪ፤ እስክትረኪ ድረስ ጠጪ። |
2. | እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን ነቅቶአል፤ የውዴ ቃል ነው፥ እርሱም ደጁን ይመታል፤ እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ መደምደሚያዬ ሆይ፥ በራሴ ጠል፥ በቈንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ ሞልቶበታልና ክፈችልኝ። |
3. | ቀሚሴን አወለቅሁ፤ እንዴት እለብሰዋለሁ? እግሬን ታጠብሁ፤ እንዴት አሳድፈዋለሁ? |
4. | ውዴ እጁን በቀዳዳ ሰደደ፥ አንጀቴም ስለ እርሱ ታወከ። |
5. | ለውዴ እከፍትለት ዘንድ ተነሣሁ፤ እጆቼ በደጅ መወርወሪያ ላይ ከርቤን አፈሰሱ፥ ጣቶቼ ፈሳሹን ከርቤ አንጠበጠቡ። |
6. | ለውዴ ከፈትሁለት፥ ውዴ ግን ፈቀቅ ብሎ አልፎ ነበር። ነፍሴ ከቃሉ የተነሣ ደነገጠች፤ ፈለግሁት፥ አላገኘሁትም፤ ጠራሁት፥ አልመለሰልኝም። |
7. | ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፤ መቱኝ፥ አቈሰሉኝም፤ ቅጥር ጠባቂዎችም የዓይነ ርግብ መሸፈኛዬን ወሰዱት። |
8. | እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ አምላችኋለሁ፤ ውዴን ያገኛችሁት እንደ ሆነ፥ እኔ ከፍቅር የተነሣ መታመሜን ንገሩት። |
9. | አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ውድሽ ማን ነው? ይህን የሚያህል አምለሽናልና ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ውድሽ ማን ነው? |
10. | ውዴ ነጭና ቀይ ነው፥ ከእልፍ የተመረጠ ነው። |
11. | ራሱ ምዝምዝ ወርቅ ነው፤ ቈንዳላው የተዝረፈረፈ ነው፥ እንደ ቁራ ጥቁረትም ጥቁር ነው። |
12. | ዓይኖቹ በሙሉ ፈሳሽ አጠገብ እንዳሉ በወተት እንደ ታጠቡ በፈሳሽ ውኃ አጠገብ እንደ ተቀመጡ እንደ ርግቦች ናቸው። |
13. | ጕንጩና ጕንጩ የሽቱ መደብ እርከን እንዳለበት እንደ ሽቱ አትክልት ናቸው፤ ከንፈሮቹ እንደ አበቦች ናቸው፥ የሚፈስስ ከርቤንም ያንጠበጥባሉ። |
14. | እጆቹ የቢረሌ ፈርጥ እንዳለበት እንደ ወርቅ ቀለበት ናቸው፤ አካሉ ብልሃተኛ እንደ ሠራው በሰንፔር እንዳጌጠ እንደ ዝሆን ጥርስ ነው። |
15. | እግሮቹ በምዝምዝ ወርቅ እንደ ተመሠረቱ እንደ ዕብነ በረድ ምሰሶች ናቸው፤ መልኩ እንደ ሊባኖስና እንደ ዝግባ ዛፍ መልካም ነው። |
16. | አፉ እጅግ ጣፋጭ ነው፥ እርሱም ፈጽሞ ያማረ ነው፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ ውዴ ይህ ነው፥ ባልንጀራዬም ይህ ነው። |
← SongOfSongs (5/8) → |