← Romans (14/16) → |
1. | በእምነት የደከመውንም ተቀበሉት፥ በአሳቡም ላይ አትፍረዱ። |
2. | ሁሉን ይበላ ዘንድ እንደ ተፈቀደለት የሚያምን አለ፥ ደካማው ግን አትክልት ይበላል። |
3. | የሚበላ የማይበላውን አይናቀው የማይበላውም በሚበላው አይፍረድ፥ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና። |
4. | አንተ በሌላው ሎሌ የምትፈርድ ማን ነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል። |
5. | ይህ ሰው አንድ ቀን ከሌላ ቀን እንዲሻል ያስባል፥ ያ ግን ቀን ሁሉ አንድ እንደ ሆነ ያስባል፤ እያንዳንዱ በገዛ አእምሮው አጥብቆ ይረዳ። |
6. | ቀንን የሚያከብር ለጌታ ብሎ ያከብራል፤ የሚበላም እግዚአብሔርን ያመሰግናልና ለጌታ ብሎ ይበላል፤ የማይበላም ለጌታ ብሎ አይበላም እግዚአብሔርንም ያመሰግናል። |
7. | ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም፤ |
8. | በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን። |
9. | ስለዚህ ነገር ሙታንንም ሕያዋንንም ይገዛ ዘንድ ክርስቶስ ሞቶአልና ሕያውም ሆኖአልና። |
10. | አንተም በወንድምህ ላይ ስለ ምን ትፈርዳለህ? ወይስ አንተ ደግሞ ወንድምህን ስለ ምን ትንቃለህ? ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና። |
11. | እኔ ሕያው ነኝ፥ ይላል ጌታ፥ ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል መላስም ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ተብሎ ተጽፎአልና። |
12. | እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን። |
13. | እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ እርስ በርሳችን አንፈራረድ፤ ይልቁን ግን ለወንድም እንቅፋትን ወይም ማሰናከያን ማንም እንዳያኖርበት ይህን ቍረጡ። |
14. | በራሱ ርኵስ የሆነ ነገር እንደ ሌለ በጌታ በኢየሱስ ሆኜ አውቄአለሁ ተረድቼአለሁም፤ ነገር ግን ምንም ርኵስ እንዲሆን ለሚቆጥር ለእርሱ ርኵስ ነው። |
15. | ወንድምህንም በመብል ምክንያት የምታሳዝን ከሆንህ እንግዲህ በፍቅር አልተመላለስህም። ክርስቶስ ስለ እርሱ የሞተለትን እርሱን በመብልህ አታጥፋው። |
16. | እንግዲህ ለእናንተ ያለው መልካም ነገር አይሰደብ፤ |
17. | የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና። |
18. | እንደዚህ አድርጎ ለክርስቶስ የሚገዛ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና፥ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው። |
19. | እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል። |
20. | በመብል ምክንያት የእግዚአብሔርን ሥራ አታፍርስ። ሁሉ ንጹሕ ነው፥ በመጠራጠር የተበላ እንደ ሆነ ግን ለዚያ ሰው ክፉ ነው። |
21. | ሥጋን አለመብላት ወይንንም አለመጠጣት ወንድምህም የሚሰናከልበትን አለማድረግ መልካም ነው። |
22. | ለአንተ ያለህ እምነት በእግዚአብሔር ፊት ለራስህ ይሁንልህ። ፈትኖ መልካም እንዲሆን በሚቈጥረው ነገር በራሱ ላይ የማይፈርድ ብፁዕ ነው። |
23. | የሚጠራጠረው ግን ቢበላ በእምነት ስላልሆነ ተኮንኖአል፤ በእምነትም ያልሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው። |
← Romans (14/16) → |