← Micah (5/7) → |
1. | የጭፍሮች ሴት ልጅ ሆይ፥ ጭፍሮችሽን አሁን ሰብስቢ፤ ከብቦ አስጨንቆናል፤ የእስራኤልን ፈራጅ ጕንጩን በበትር ይመታሉ። |
2. | አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል። |
3. | ስለዚህ ወላጂቱ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ የቀሩትም ወንድሞቹ ወደ እስራኤል ልጆች ይመለሳሉ። |
4. | እርሱም ይቆማል፥ በእግዚአብሔርም ኃይል በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ግርማ መንጋውን ይጠብቃል፤ እነርሱም ይኖራሉ፤ እርሱ አሁን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ ይሆናልና። |
5. | ይህም ለሰላም ይሆናል፤ አሦራዊውም ወደ አገራችን በገባ ጊዜ፥ ምድራችንንም በረገጠ ጊዜ ሰባት እረኞችና ስምንት አለቆች እናስነሣበታለን። |
6. | የአሦርንም አገር በሰይፍ፥ የናምሩድንም አገር በመግቢያው ውስጥ ያፈርሳሉ፤ አሦራዊውም ወደ አገራችን በገባ ጊዜ፥ ዳርቾቻችንንም በረገጠ ጊዜ እርሱ ይታደገናል። |
7. | የያዕቆብም ቅሬታ በብዙ አሕዛብ መካከል ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚወርድ ጠል፥ በሣር ላይ እንደሚወድ ካፊያ፤ ሰውንም እንደማይጠብቅ፥ የሰውንም ልጆች ተስፋ እንደማያደርግ ይሆናል። |
8. | በዱር አራዊትም መካከል እንዳለ አንበሳ፥ በበጎች መንጋም መካከል አልፎ እንደሚረግጥ፥ የሚታደግም ሳይኖር እንደሚነጥቅ እንደ አንበሳ ደቦል፥ እንዲሁ የያዕቆብ ቅሬታ በአሕዛብና በብዙ ወገኖች መካከል ይሆናል። |
9. | እጅህ በጠላቶችህ ላይ ከፍ ከፍ ትበል፥ ጠላቶችህም ሁሉ ይጥፉ። |
10. | በዚያም ቀን ፈረሶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ሰረገሎችህንም እሰብራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ |
11. | የምድርህንም ከተሞች አጠፋለሁ፥ ምሽጎችህንም ሁሉ አፈርሳለሁ፤ |
12. | መተትንም ከእጅህ አጠፋለሁ፥ ምዋርተኞችም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆኑልህም፤ |
13. | የተቀረጹትን ምስሎችህንና ሐውልቶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ለእጅህም ሥራ ከእንግዲህ ወዲህ አትሰግድም፤ |
14. | የማምለኪያ ዐፀዶችህንም ከመካከልህ እነቅላለሁ፥ ከተሞችህንም አፈርሳለሁ። |
15. | ባልሰሙም አሕዛብ ላይ በቍጣና በመዓት እበቀላለሁ። |
← Micah (5/7) → |