← Luke (15/24) → |
1. | ቀራጮችና ኃጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር። |
2. | ፈሪሳውያንና ጻፎችም። ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል ብለው እርስ በርሳቸው አንጐራጐሩ። |
3. | ይህንም ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል። |
4. | መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? |
5. | ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ |
6. | ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ። የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል። |
7. | እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል። |
8. | ወይም አሥር ድሪም ያላት አንድ ድሪም ቢጠፋባት፥ መብራት አብርታ ቤትዋንም ጠርጋ እስክታገኘው ድረስ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት? |
9. | ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጐረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ። የጠፋውን ድሪሜን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ትላቸዋለች። |
10. | እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል። |
11. | እንዲህም አለ። አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። |
12. | ከእነርሱም ታናሹ አባቱን። አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። |
13. | ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ ከዚያም እያባከነ ገዘቡን በተነ። |
14. | ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። |
15. | ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው። |
16. | እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም። |
17. | ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ። እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። |
18. | ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ |
19. | ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ። |
20. | ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። |
21. | ልጁም። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው። |
22. | አባቱ ግን ባሪያዎቹን አለ። ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤ |
23. | የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤ |
24. | ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይላቸው ጀመር። |
25. | ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የመሰንቆና የዘፈን ድምፅ ሰማ፤ |
26. | ከብላቴናዎችም አንዱን ጠርቶ። ይህ ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀ። |
27. | እርሱም። ወንድምህ መጥቶአልና በደኅና ስላገኘው አባትህ የሰባውን ፊሪዳ አረደለት አለው። |
28. | ተቈጣም ሊገባም አልወደደም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው። |
29. | እርሱ ግን መልሶ አባቱን። እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጥቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ |
30. | ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፊሪዳ አረድህለት አለው። |
31. | እርሱ ግን። ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፥ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ |
32. | ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል አለው። |
← Luke (15/24) → |