← Luke (10/24) → |
1. | ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎቹን ሰብዓ ሾመ፥ ሁለት ሁለትም አድርጎ እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ በፊቱ ላካቸው። |
2. | አላቸውም። መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዴህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት። |
3. | ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ። |
4. | ኮረጆም ከረጢትም ጫማም አትያዙ፤ በመንገድም ለማንም እጅ አትንሡ። |
5. | ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ። ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። |
6. | በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል። |
7. | በዚያም ቤት ከእነርሱ ዘንድ ካለው እየበላችሁና እየጠጣችሁ ተቀመጡ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና። ከቤት ወደ ቤት አትተላለፉ። |
8. | ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሉአችሁ፥ ያቀረቡላችሁን ብሉ፤ |
9. | በእርስዋም ያሉትን ድውዮችን ፈውሱና። የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች በሉአቸው። |
10. | ነገር ግን ወደምትገቡባት ከተማ ሁሉ ባይቀበሉአችሁ፥ ወደ አደባባይዋ ወጥታችሁ። |
11. | ከከተማችሁ የተጣበቀብንን ትቢያ እንኳን እናራግፍላችኋለን፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን እወቁ በሉ። |
12. | እላችኋለሁ፥ በዚያን ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል። |
13. | ወዮልሽ ኮራዚን፥ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው በአመድም ተቀምጠው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበር። |
14. | ነገር ግን በፍርድ ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። |
15. | አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ። |
16. | የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፥ እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል፤ እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል። |
17. | ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው። ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት። |
18. | እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። |
19. | እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። |
20. | ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ። |
21. | በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አደረገና። የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግናለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። |
22. | ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፥ ወልድንም ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፥ አብንም ማን እንደ ሆነ ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር የሚያውቅ የለም አለ። |
23. | ወደ ደቀ መዛሙርቱም ዘወር ብሎ ለብቻቸው። የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው። |
24. | እላችኋለሁና፥ እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወድደው አልሰሙም አለ። |
25. | እነሆም፥ አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው ተነሥቶ። መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? አለው። |
26. | እርሱም በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ? አለው። |
27. | እርሱም መልሶ። ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። |
28. | ኢየሱስም። እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ አለው። |
29. | እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን። ባልንጀራዬስ ማን ነው? አለው። |
30. | ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ። አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። |
31. | ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። |
32. | እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። |
33. | አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፥ |
34. | ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቍስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም። |
35. | በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና። ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው። |
36. | እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል? |
37. | እርሱም። ምሕረት ያደረገለት አለ። ኢየሱስም። ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ አለው። |
38. | ሲሄዱም እርሱ ወደ አንዲት መንደር ገባ፤ ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤትዋ ተቀበለችው። |
39. | ለእርስዋም ማርያም የምትባል እኅት ነበረቻት፥ እርስዋም ደግሞ ቃሉን ልትሰማ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ነበረች። |
40. | ማርታ ግን አገልግሎት ስለ በዛባት ባከነች፤ ቀርባም። ጌታ ሆይ፥ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አይገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት አለችው። |
41. | ኢየሱስም መልሶ። ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ |
42. | የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት። |
← Luke (10/24) → |