← Joshua (2/24) → |
1. | የነዌም ልጅ ኢያሱ። ሄዳችሁ ምድሪቱንና ኢያሪኮን እዩ ብሎ ከሰጢም ሁለት ሰላዮች በስውር ላከ። ሄዱም፤ ረዓብም ወደሚሉአት ጋለሞታ ቤት ገቡ፥ በዚያም አደሩ። |
2. | የኢያሪኮም ንጉሥ። እነሆ፥ ሰዎች ከእስራኤል ልጆች አገሩን ሊሰልሉ ወደዚህ በሌሊት ገቡ ሲባል ወሬ ሰማ። |
3. | የኢያሪኮም ንጉሥ። አገሩን ሁሉ ሊሰልሉ መጥተዋልና ወደ አንቺ የመጡትን ወደ ቤትሽም የገቡትን ሰዎች አውጪ ብሎ ወደ ረዓብ ላከ። |
4. | ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፤ እርስዋም። አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፥ ከወዴት እንደ ሆኑ ግን አላወቅሁም፤ |
5. | በሩም ሲዘጋ ሲጨልምም ሰዎቹ ወጡ፤ ወዴት እንደ ሄዱ አላውቅም፤ ፈጥናችሁ አሳድዱአቸው፥ ታገኙአቸውማላችሁ አለች። |
6. | እርስዋ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታቸው ነበር፤ በዚያም በረበረበችው በተልባ እግር ውስጥ ሸሽጋቸው ነበር። |
7. | ሰዎቹም ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ በሚወስደው መንገድ አሳደዱአቸው፤ እሳዳጆችም ከወጡ በኋላ በሩ ተቈለፈ። |
8. | እነዚህም ሳይተኙ ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። |
9. | ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው። እግዚአብሔር ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ፥ እናንተንም መፍራት በላያችን እንደ ወደቀ፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ እንደ ቀለጡ አወቅሁ። |
10. | ከግብፅ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። |
11. | ይህንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተንሣ ከዚያ ወዲያ ለማንም ነፍስ አልቀረለትም። |
12. | አሁንም፥ እባካችሁ፥ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፥ በእውነትም ምልክት ስጡኝ፥ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደ ሠራሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት እንድትሠሩ፥ |
13. | አባቴንና እናቴንም ወንድሞቼንና እኅቶቼንም ያላቸውንም ሁሉ እንድታድኑ፥ ሰውነታችንንም ከሞት እንድታድኑ። |
14. | ሰዎቹም። ይህን ነገራችንን ባትገልጪ ነፍሳችን በነፍሳችሁ ፋንታ ለሞት ይሆናል፤ እግዚአብሔርም ምድሪቱን በሰጠን ጊዜ ከአንቺ ጋር ቸርነትንና እውነትን እናደርጋለን አሉአት። |
15. | ቤትዋም በከተማ ቅጥር የተጠጋ ነበረና፥ እርስዋም በቅጥሩ ላይ ተቀምጣ ነበርና ከመስኮቱ በገመድ አወረደቻቸው። |
16. | እርስዋም። አሳዳጆቹ እንዳያገኙአችሁ ወደ ተራራው ሂዱ፤ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ በዚያ ሦስት ቀን ተሰውራችሁ ተቀመጡ፤ ኋላም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ አለቻቸው። |
17. | ሰዎቹም አሉአት። እኛ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሐን እንሆናለን። |
18. | እነሆ፥ እኛ ወደ አገሩ በገባን ጊዜ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረድሽበት መስኮት በኩል እሰሪው፤ አባትሽንም እናትሽንም ወንድሞችሽንም የአባትሽንም ቤተ ሰብ ሁሉ ወደ አንቺ ወደ ቤትሽ ሰብስቢ። |
19. | ከቤትሽም ደጅ ወደ ሜዳ የሚወጣ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፥ እኛም ንጹሐን እንሆናለን፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋር በቤቱ ውስጥ ያለውን አንድ እጅ ቢነካው ደሙ በእኛ ራስ ላይ ይሆናል። |
20. | ይህንን ነገራችንን ግን ብትገልጪ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሐን እንሆናለን። |
21. | እርስዋም። እንደ ቃላችሁ ይሁን አለች፤ ሰደደቻቸውም እነርሱም ሄዱ፤ ቀዩንም ፈትል በመስኮቱ በኩል አንጠለጠለችው። |
22. | እነርሱም ሄደው ወደ ተራራው ደረሱ፥ አሳዳጆቹም እስኪመለሱ ድረስ ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጡ፤ አሳዳጆቹም በመንገዱ ሁሉ ፈልገው አላገኙአቸውም። |
23. | ሁለቱም ሰዎች ተመለሱ፥ ከተራራውም ወርደው ተሻገሩ፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ መጡ፤ የደረሰባቸውንም ሁሉ አወሩለት። |
24. | ኢያሱንም። በእውነት እግዚአብሔር አገሩን ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአል፤ በአገሩም ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ በፊታችን ይቀልጣሉ አሉት። a |
← Joshua (2/24) → |