| ← Isaiah (16/66) → |
| 1. | በምድርም ላይ ለሠለጠነው አለቃ የበግ ጠቦቶችን በምድረ በዳ ካለችው ከሴላ ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ ስደዱ። |
| 2. | እንደሚበርር ወፍ እንደ ተበተኑም ጫጩቶች እንዲሁ የሞዓብ ሴቶች ልጆች በአርኖን መሻገሪያዎች ይሆናሉ። |
| 3. | ምክርን ምከሪ፥ ፍርድን አድርጊ፥ በቀትር ጊዜ ጥላሽን እንደ ሌሊት አድርጊ፤ የተሰደዱትን ሸሽጊ፥ የሸሹትን አትግለጪ። |
| 4. | ከሞዓብ የተሰደዱት ከአንቺ ጋር ይቀመጡ፤ ከሚያጠፋቸው ፊት መጋረጃ ሁኛቸው። የሚያስጨንቁ አልቀዋል፥ ጥፋትም ቀርቶአል፤ ይጨቍኑ የነበሩ ከምድር ጠፍተዋል። |
| 5. | ዙፋንም በምሕረት ይቀናል፥ በዚያም ላይ በዳዊት ድንኳን ፍርድን የሚሻ ጽድቅንም የሚያፈጥን ፈራጅ በእውነት ይቀመጣል |
| 6. | ስለ ሞዓብ ትዕቢት እጅግ ስለ መታበዩ፥ ስለ ኵራቱና ስለ ትዕቢቱ ስለ ቍጣውም ሰምተናል፤ ትምሕክቱ ከንቱ ነው። |
| 7. | ስለዚህ ሞዓብ ስለ ሞዓብ ዋይ ይላል፤ ሁሉም ዋይ ይላል፤ ስለ ቂርሐራሴት መሠራት በጥልቅ ኀዘን ታለቅሳላችሁ። |
| 8. | የሐሴቦን እርሻዎችና የሴባማ ወይን ግንዶች አዝነዋል። የአሕዛብ አለቆች የሰባበሩአቸው ቅርንጫፎች እስከ ኢያዜር ደርሰው ወደ ምድረ በዳ ወጥተው ነበር፤ ቍጥቋጦቹም ተዘርግተው ባሕርን ተሻግረው ነበር። |
| 9. | ስለዚህ በኢያዜር ልቅሶ ስለ ሴባማ ወይን ግንድ አለቅሳለሁ፤ ሐሴቦንና ኤልያሊ ሆይ፥ በዛፍሽ ፍሬና በወይንሽ መከር የጦር ጩኸት ወድቆአልና በእንባዬ አረካሻለሁ። |
| 10. | ደስታና ሐሤትም ከፍሬያማው እርሻ ተወስዶአል፥ በወይኑም ቦታዎች ዝማሬና እልልታ የለም፤ በመጥመቂያም ወይን የሚረግጥ የለም፤ የረጋጮቹን እልልታ አጥፍቻለሁ። |
| 11. | ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ አንጀቴም ስለ ቂርሔሬስ እንደ መሰንቆ ትጮኻለች። |
| 12. | ሞዓብም መጥቶ በኮረብታ መስገጃ ላይ በደከመና ለጸሎት ወደ መቅደሱ በገባ ጊዜ አያሸንፍም |
| 13. | እግዚአብሔር በሞዓብ ላይ በድሮ ዘመን የተናገረው ነገር ይህ ነው። |
| 14. | አሁን ግን እግዚአብሔር። በሦስት ዓመት ውስጥ እንደ ምንደኛ ዓመት የሞዓብ ክብርና የሕዝቡ ሁሉ ብዛት ይዋረዳል፥ ቅሬታውም እጅግ ያነሰና የተጠቃ ይሆናል ይላል። |
| ← Isaiah (16/66) → |