| ← Hosea (8/14) → |
| 1. | መለከትን ወደ አፍህ አቅርብ፤ ቃል ኪዳኔን ተላልፈዋልና፥ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ንስር ይመጣል። |
| 2. | እነርሱም። አምላክ ሆይ፥ እኛ እስራኤል አወቅንህ ብለው ወደ እኔ ይጮኻሉ። |
| 3. | እስራኤል ደግነትን ጥሎአል፤ ጠላትም ያሳድዱታል። |
| 4. | ለራሳቸው ነገሥታትን አነገሡ፥ ከእኔም ዘንድ አይደለም፤ አለቆችንም አደረጉ፥ እኔም አላወቅሁም፤ ለጥፋታቸውም ከብራቸውና ከወርቃቸው፤ ጣዖታትን ለራሳቸው አደረጉ። |
| 5. | ሰማርያ ሆይ፥ እምቦሳህን፤ ጥሎአል፤ ቍጣዬ በላያቸው ነድዶአል፤ እስከ መቼ ድረስ ንጹሕ ሊሆኑ አይችሉም? |
| 6. | ይህ ደግሞ ከእስራኤል ዘንድ ነው፤ ሠራተኛ ሠራው፥ እርሱም አምላክ አይደለም፤ የሰማርያም እምቦሳ ይቈራረጣል። |
| 7. | ነፍስን ዘርተዋል፥ ዐውሎ ነፍስንም ያጭዳሉ፤ አገዳ የለውም፥ ከፍሬውም ዱቄት አይገኝም፤ ቢገኝም እንግዶች ይበሉታል። |
| 8. | እስራኤል ተውጦአል፥ በአሕዛብም መካከል ዛሬ እንደ ረከሰ ዕቃ ሆኖአል። |
| 9. | ለብቻውም እንደሚቀመጥ እንደ ምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥተዋል፤ ኤፍሬምም ወዳጆቹን በእጅ መንሻ ገዛ። |
| 10. | ነገር ግን ለአሕዛብ እጅ መንሻ ቢሰጡ እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፤ ከንጉሥና ከአለቆችም ሸክም የተነሣ ይደክማሉ። |
| 11. | ኤፍሬም ኃጢአትን ለመሥራት መሠዊያ አብዝቶአልና መሠዊያ ለኃጢአት ይሆንለታል። |
| 12. | የሕጌን ብዛት ጽፌለታለሁ፤ እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጥረውታል። |
| 13. | መሥዋዕቴን ያቀርባሉ፥ ሥጋንም ያርዳሉ፥ ይበላሉም፤ እግዚአብሔር ግን አይቀበላቸውም፤ በደላቸውንም ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይቀጣል፤ እነርሱም ወደ ግብጽ ይመለሳሉ። |
| 14. | እስራኤል ፈጣሪውን ረስቶአል፥ መስገጃዎችንም ሠርቶአል፤ ይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች አብዝቶአል፤ እኔ ግን በከተሞች ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችንም ትበላለች። |
| ← Hosea (8/14) → |