← Genesis (19/50) → |
1. | ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ፤ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ፤ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፥ አላቸውም። |
2. | ጌቶቼ ሆይ፥ ወደ ባሪያችሁ ቤት አቅኑ፥ ከዚያም እደሩ፥ እግራችሁንም ታጠቡ፤ ነገ ማልዳችሁም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ። እነርሱም። በአደባባዩ እናድራለን እንጂ፥ አይሆንም አሉት። |
3. | እጅግም ዘበዘባቸው፤ ወደ እርሱም አቀኑ፥ ወደ ቤቱም ገቡ፤ ማዕድ አቀረበላቸው፥ ቂጣንም ጋገረ እነርሱም በሉ። |
4. | ገናም ሳይተኙ የዚያች ከተማ የሰዶም ሰዎች፥ ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ በየስፍራው ያለው ሕዝብ ሁሉ፥ ቤቱን ከበቡት። |
5. | ሎጥንም ጠርተው እንዲህ አሉት። በዚህ ሌሊት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች ወዴት ናቸው? እናውቃቸው ዘንድ ወደ እኛ አውጣቸው። |
6. | ሎጥም ወደ እነርሱ ወደ ደጅ ወጣ መዝጊያውንም በኋላው ዘጋው፤ |
7. | እንዲህም አለ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር አታድርጉ፤ |
8. | እነሆ፥ ወንድን ያላወቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ፤ እነርሱን ላውጣላችሁ፥ እንደ ወደዳችሁም አድርጓቸው፤ በእነዚህ ሰዎች ብቻ ምንም አታድርጉ፥ እነርሱ በጣራዬ ጥላ ሥር ገብተዋልና። |
9. | እነርሱም። ወዲያ ሂድ አሉት። ደግሞም እንዲህ አሉ። ይህ ሰው በእንግድነት ለመኖር መጣ፥ ፍርዱንም ይፈርድ ዘንድ ይፈልጋል፤ አሁን በአንተ ከእነርሱ ይልቅ ክፉ እናደርግብሃለን። ሎጥንም እጅግ ተጋፉት፥ የደጁንም መዝጊያ ለመስበር ቀረቡ። |
10. | ሁለቱም ሰዎች እጃቸውን ዘርግተው ሎጥን ወደ እነርሱ ዘንድ ወደ ቤት አገቡት መዝጊያውንም ዘጉት። |
11. | በቤቱ ደጃፍ የነበሩትንም ሰዎች ከታናሻቸው ጀምሮ እስከ ታለቃቸው ድረስ አሳወሩአቸው፤ ደጃፉንም ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ። |
12. | ሁለቱም ሰዎች ሎጥን አሉት። ከዚህ ሌላ ማን አለህ? አማችም ቢሆን ወንድ ልጅም ቢሆን ወይም ሴት ልጅ ብትሆን በከተማይቱ ያለህን ሁሉ ከዚህ ስፍራ አስወጣቸው፤ |
13. | እኛ ይህን ስፍራ እናጠፋለንና፥ ጩኸታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና፤ እናጠፋውም ዘንድ እግዚአብሔር ሰድዶናል። |
14. | ሎጥም ወጣ፥ ልጆቹን ለሚያገቡት ለአማቾቹም ነገራቸው፥ አላቸውም። ተነሡ፤ ከዚህ ስፍራ ውጡ፤ እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ያጠፋልና። ለአማቾቹ ግን የሚያፌዝባቸው መሰላቸው። |
15. | ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን። ተነሣ፥ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፤ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ እያሉ ያስቸኵሉት ነበር። |
16. | እርሱም በዘገየ ጊዜ እግዚአብሔር ስላዘነለት እነዚያ ሰዎች የእርሱን እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት። |
17. | ወደ ሜዳም ካወጡአቸው በኋላ እንዲህ አለው። ራስህን አድን፤ ወደ ኋላህ አትይ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ። |
18. | ሎጥም፤ አላቸው። ጌቶቼ ሆይ፥ እንዲህስ አይሁን፤ |
19. | እነሆ ባሪያህ በፊትህ ሞገስን አግኝቶአል፥ ነፍሴን ለማዳን ያደረግህልኝን ምሕረትህንም አብዝተሃል፤ ክፉ እንዳያገኘኝና እንዳልሞት ወደ ተራራ ሸሽቼ አመልጥ ዘንድ አልችልም፤ |
20. | እነሆ ይህች ከተማ ወደ እርስዋ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት፥ እርስዋም ትንሽ ናት፤ ነፍሴን ለማዳን ወደ እርስዋ ሸሽቼ ላምልጥ፤ እርስዋ ትንሽ ከተማ አይደለችምን? |
21. | እርሱም አለው። የተናገርሃትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንኸኝን ተቀብዬሃለሁ፤ |
22. | በቶሎ ወደዚያ ሸሽትህ አምልጥ፤ ወደዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም አደርግ ዘንድ አልችልምና። ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር ተባለ። |
23. | ሎጥ ወደ ዞዓር በገባ ጊዜ ፀሐይ በምድር ላይ ወጣች። |
24. | እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤ |
25. | እነዚያንም ከተሞች፥ በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ፥ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሁሉ፥ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ። |
26. | የሎጥም ሚስት ወደ ኋላዋ ተመለከተች፥ የጨው ሐውልትም ሆነች። |
27. | አብርሃምም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ወደ ነበረበት ስፍራ ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፤ |
28. | ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ በዚያች አገር ወዳለውም ምድር ሁሉ ተመለከተ፤ እነሆም የአገሪቱ ጢስ እንደ እቶን ጢስ ሲነሣ አየ። |
29. | እግዚአብሔርም እነዚያን የአገር ከተሞች ባጠፋ ጊዜ አብርሃምን አሰበው፤ ሎጥ ተቀምጦበት የነበረውንም ከተማ ባጠፋ ጊዜ ከዚያ ጥፋት መካከል ሎጥን አወጣው። |
30. | ሎጥም ከዞዓር ወጣ፤ በዞዓር ይቀመጥ ዘንድ ስለ ፈራም ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር በተራራ ተቀመጠ፤ በዋሻም ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር ተቀመጠ። |
31. | ታላቂቱም ታናሺቱን አለቻት። አባታችን ሸመገለ፥ በምድርም ሁሉ እንዳለው ልማድ ሊገናኘን የሚችል ሰው ከምድር ላይ የለም፤ |
32. | ነዪ አባታቻንንም የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእርሱ ጋር እንተኛ፥ ከአባታችንም ዘር እናስቀር። |
33. | በዚያችም ሌሊት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ታላቂቱም ገባች፥ ከአባትዋም ጋር ተኛች፤ እርሱም ስትተኛና ስትነሣ አላወቀም። |
34. | በነጋውም ታላቂቱ ታናሺቱን አለቻት። እነሆ ትናንት ከአባቴ ጋር ተኛሁ፤ ዛሬ ሌሊት ደግሞ የወይን ጠጅ እናጠጣው አንቺም ግቢና ከእርሱ ጋር ተኚ፥ ከአባታችንም ዘር እናስቀር። |
35. | አባታቸውንም በዚያች ሌሊት ደግሞ የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ታናሺቱም ገብታ ከእርሱ ጋር ተኛች፤ እርሱም ስትተኛና ስትነሣ አላወቀም። |
36. | የሎጥም ሁለቱ ሴቶች ልጆች ከአባታቸው ፀነሱ። |
37. | ታላቂቱም ወንድ ልጅ ወለደች ስሙንም ሞዓብ ብላ ጠራችው፤ እርሱም እስከ ዛሬ የሞዓባውያን አባት ነው። |
38. | ታናሺቱም ደግሞ ወንድ ልጅ ወለደች ስሙንም። የወገኔ ልጅ ስትል አሞን ብላ ጠራችው፤ እርሱም እስከ ዛሬ የአሞናውያን አባት ነው። |
← Genesis (19/50) → |