| ← Galatians (6/6) |
| 1. | ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። |
| 2. | ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ። |
| 3. | አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና። |
| 4. | ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ |
| 5. | እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና። |
| 6. | ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል። |
| 7. | አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ |
| 8. | በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። |
| 9. | ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት። |
| 10. | እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ። |
| 11. | እንዴት ባሉ ታላላቆች ፊደላት በእጄ እንደ ጻፍሁላችሁ እዩ። |
| 12. | በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው። |
| 13. | በሥጋችሁ እንዲመኩ ልትገረዙ ይወዳሉ እንጂ የተገረዙቱ ራሳቸው እንኳ ሕግን አይጠብቁም። |
| 14. | ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። |
| 15. | በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። |
| 16. | በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። |
| 17. | እኔ የኢየሱስን ማኅተም በሥጋዬ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ። |
| 18. | ወንድሞች ሆይ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን። አሜን። |
| ← Galatians (6/6) |