| ← Galatians (4/6) → |
| 1. | ነገር ግን እላለሁ፥ ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ምንም የሁሉ ጌታ ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም፥ |
| 2. | ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው። |
| 3. | እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን፤ |
| 4. | ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ |
| 5. | እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። |
| 6. | ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። |
| 7. | ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ። |
| 8. | ነገር ግን በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን ሳታውቁ በባሕርያቸው አማልክት ለማይሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ተገዛችሁ፤ |
| 9. | አሁን ግን እግዚአብሔርን ስታውቁ ይልቅስ በእግዚአብሔር ስትታወቁ እንደ ገና ወደ ደካማ ወደሚናቅም ወደ መጀመሪያ ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? እንደ ገና ባሪያዎች ሆናችሁ ዳግመኛ ለዚያ ልትገዙ ትወዳላችሁን? |
| 10. | ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ። |
| 11. | ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለሁ ብዬ እፈራችኋለሁ። |
| 12. | ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ሆኜአለሁና። እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ። አንዳችም አልበደላችሁኝም። |
| 13. | በመጀመሪያ ወንጌልን በሰበክሁላችሁ ጊዜ ከሥጋ ድካም የተነሣ እንደ ነበረ ታውቃላችሁ፥ |
| 14. | በሥጋዬም ፈተና የሆነባችሁን ነገር አልናቃችሁትምና አልተጸየፋችሁትም ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ አዎን እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ። |
| 15. | እንግዲህ ደስ ማሰኘታችሁ ወዴት አለ? ቢቻልስ ዓይኖቻችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ። |
| 16. | እንኪያስ እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን? |
| 17. | በብርቱ ይፈልጉአችኋል፥ ለመልካም አይደለም ነገር ግን በብርቱ ትፈልጉአቸው ዘንድ በውጭ ሊያስቀሩአችሁ ይወዳሉ። |
| 18. | ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ በምኖርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ በመልካም ነገር ተፈላጊ ብትሆኑ መልካም ነው። |
| 19. | ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል። |
| 20. | ስለ እናንተ አመነታለሁና አሁን በእናንተ ዘንድ ሆኜ ድምፄን ልለውጥ በወደድሁ። |
| 21. | እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፥ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ። |
| 22. | አንዱ ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት ተጽፎአልና። |
| 23. | ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአል፥ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዶአል። |
| 24. | ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት። |
| 25. | ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና። |
| 26. | ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት። |
| 27. | አንቺ የማትወልጅ መካን፥ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፥ እልል በዪና ጩኺ፤ ባል ካላቱ ይልቅ የብቸኛይቱ ልጆች በዝተዋልና ተብሎ ተጽፎአል። |
| 28. | እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን። |
| 29. | ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። |
| 30. | ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት። |
| 31. | ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም። |
| ← Galatians (4/6) → |