← Deuteronomy (5/34) → |
1. | ሙሴም እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ አላቸው። እስራኤል ሆይ፥ እንድትማሩአት በማድረግም እንድትጠብቁአት ዛሬ በጆሮአችሁ የምናገራትን ሥርዓትና ፍርድ ስሙ። |
2. | አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። |
3. | እግዚአብሔር ዛሬ በዚህ በሕይወት ካለነው ከእኛ ከሁላችን ጋር እንጂ ከአባቶቻችን ጋር ይህችን ቃል ኪዳን አላደረገም። |
4. | በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔር ፊት ለፊት ተናገራችሁ። |
5. | እኔ የእግዚአብሔርን ቃል እነግራችሁ ዘንድ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔርና በእናንተ መካከል ቆሜ ነበር፤ እናንተ በእሳቱ ምክንያት ፈርታችኋልና፥ ወደ ተራራውም አልወጣችሁምና። እርሱም አለ። |
6. | ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። |
7. | ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። |
8. | በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፤ |
10. | በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤ ለሚወድዱኝ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኛና አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም። |
11. | የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና። |
12. | እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ ጠብቅ። |
13. | ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፥ |
14. | ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር አምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ እንደምታርፍ ሎሌህና ገረድህ ያርፉ ዘንድ፥ አንተ ወንድ ልጅህም ሴት ልጅህም ሎሌህም ገረድህም በሬህም አህያህም ከብትህም ሁሉ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ። |
15. | አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ እግዚአብሔር አምላክህ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ ከዚያ አወጣህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ የሰንበትን ቀን ትጠብቅ ዘንድ አዘዘህ። |
16. | እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፥ መልካምም እንዲሆንልህ። |
17. | አትግደል። |
18. | አታመንዝር። |
19. | አትስረቅ። |
20. | በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። |
21. | የባልጀራህን ሚስት አትመኝ፤ የባልንጀራህንም ቤት እርሻውንም ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም፥ ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ። |
22. | እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳትና በደመናው በጨለማውም ውስጥ ሆኖ በታላቅ ድምፅ እነዚህን ቃሎች ለጉባኤአችሁ ሁሉ ተናገረ፤ ምንም ምን አልጨመረም። በሁለቱም የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው፥ ለእኔም ሰጣቸው። |
23. | ተራራው በእሳት ሲነድድ ከጨለማው ውስጥ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ፥ እናንተ፥ የነገዶቻችሁ አለቆች ሽማግሌዎቻችሁም፥ ወደ እኔ ቀረባችሁ፤ |
24. | አላችሁም። እነሆ፥ አምላካችን እግዚአብሔር ክብሩንና ታላቅነቱን አሳይቶናል፥ ከእሳቱም ውስጥ ድምፁን ሰምተናል፤ እግዚአብሔርም ከሰው ጋር ሲነጋገር ሰውዮውም በሕይወት ሲኖር ዛሬ አይተናል። |
25. | አሁን እንግዲህ ይህች ታላቂቱ እሳት ታቃጥለናለችና ለምን እንሞታለን? እኛ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ድምፅ ደግሞ ብንሰማ እንሞታለን። |
26. | ከሥጋ ለባሽ ሁሉ እኛ እንደ ሰማን በእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የሕያው አምላክን ድምፅ ሰምቶ በሕይወቱ የኖረ ማን ነው? |
27. | አንተ ቅረብ፥ አምላካችን እግዚአብሔር የሚለውን ሁሉ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔርም ለአንተ የሚናገረውን ሁሉ ለእኛ ንገረን፤ እኛም ሰምተን እናደርገዋለን። |
28. | በተናገራችሁኝም ጊዜ እግዚአብሔር የእናንተን ቃል ጽምፅ ሰማ፤ እግዚአብሔርም አለኝ። ይህ ሕዝብ የተናገሩህን ቃል ድምፅ ሰምቼአለሁ፤ የተናገሩህ ሁሉ መልካም ነገር ነው። |
29. | ለእነርሱም ለዘላለምም ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ፥ እንዲፈሩኝ ሁልጊዜም ትእዛዜን ሁሉ እንዲጠብቁ እንዲህ ያለ ልብ ምነው በሆነላቸው! |
30. | ሄደህ። ወደ ድንኳናችሁ ተመለሱ በላቸው። |
31. | አንተ ግን በዚህ በእኔ ዘንድ ቁም፥ ርስት አድርጌ በምሰጣቸውም ምድር ላይ ያደርጉአት ዘንድ የምታስተምራቸውን ትእዛዜንና ሥርዓቴን ፍርዴንም ሁሉ እነግርሃለሁ። |
32. | እግዚአብሔር አምላካችሁ እንዳዘዛችሁ ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ። |
33. | በሕይወት እንድትኖሩ፥ መልካምም እንዲሆንላችሁ፥ በምትወርሱአትም ምድር ዕድሜአችሁ እንዲረዝም፥ እግዚአብሔር አምላካችሁ ባዘዛችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ። |
← Deuteronomy (5/34) → |