← Deuteronomy (24/34) → |
1. | ሰው ሴትን ወስዶ ቢያገባ፥ የእፍረት ነገር ስላገኘባት በእርሱ ዘንድ ሞገስ ባታገኝ፥ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ይስጣት፥ ከቤቱም ይስደዳት። |
2. | ከቤቱም ከወጣች በኋላ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ |
3. | ሁለተኛውም ባል ቢጠላት፥ የፍችዋንም ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ቢሰጣት፥ ከቤቱም ቢሰድዳት፥ ወይም ሚስት አድርጎ ያገባት ሁለተኛው ባልዋ ቢሞት፥ |
4. | የሰደዳት የቀድሞ ባልዋ ከረከሰች በኋላ ደግሞ ያገባት ዘንድ አይገባውም፤ ያ በእግዚአብሔር የተጠላ ነው፤ አምላክህም እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር አታርክስ። |
5. | አዲስ ሚስትም ያገባ ሰው ወደ ጦርነት አይሂድ፥ ነገርም አይጫኑበት፤ ነገር ግን አንድ ዓመት በቤቱ በፈቃዱ ይቀመጥ፥ የወሰዳትንም ሚስቱን ደስ ያሰኛት። |
6. | የሰውን ነፍስ እንደ መውሰድ ነውና ወፍጮ ወይም መጅ ስለ መያዣ ማንም አይውሰድ። |
7. | ማንም ሰው ከእስራኤል ልጆች ከወንድሞቹ አንዱን ሰርቆ እንደ ባሪያ ሲያደርግበት ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፥ ያ ሌባ ይሙት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ። |
8. | በለምጽ ደዌ ሌዋውያን ካህናት ያስተማሩህን ሁሉ ፈጽመህ እንድትጠብቅ እንድታደርግም ተጠንቀቅ፤ እኔ ያዘዝኋቸውን እንዲሁ ታደርግ ዘንድ ጠብቅ። |
9. | አምላክህ እግዚአብሔር ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ በመንገድ ሳላችሁ በማርያም ላይ ያደረገውን አስብ። |
10. | ለባልንጀራህ ባበደርኸው ጊዜ መያዣውን ልትወስድ ወደ ቤቱ አትግባ። |
11. | አንተ በውጭ ቁም ያበደርኸውም ሰው መያዣውን ያውጣልህ። |
12. | ያም ሰው ድሃ ቢሆን መያዣውን በአንተ ዘንድ አታሳድር። |
13. | ለብሶት እንዲተኛ እንዲባርክህም ፀሐይ ሳይገባ መያዣውን ፈጽመህ መልስለት፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ጽድቅ ይሆንልሃል |
14. | ድሀና ችግረኛ የሆነውን ምንደኛ፥ ከወንድሞችህ ወይም በምድርህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ከሚቀመጡት መጻተኞች ቢሆን፥ አታስጨንቀው። |
15. | ድሀ ነውና፥ ነፍሱም ጠንክራ ትፈልገዋለችና ወደ እግዚአብሔር እንዳይጮኽብህ ኃጢአትም እንዳይሆንብህ ደመወዙን ፀሐይ ሳይገባ በቀኑ ስጠው። |
16. | አባቶች ስለ ልጆች አይገደሉ፥ ልጆችም ስለ አባቶች አይገደሉ፤ ነገር ግን ሁሉ እያንዳንዱ በኃጢአቱ ይገደል። |
17. | የመጻተኛውንና የድሀ አደጉን ፍርድ አታጣምምባቸው፤ የመበለቲቱን ልብስ ለመያዣ አትውሰድባት። |
18. | አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ከዚያ እንዳዳነህ አስብ፤ ስለዚህ ይህን ነገር ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ። |
19. | የእርሻህን መከር ባጨድህ ጊዜ ነዶም ረስተህ በእርሻህ ብታስቀር፥ ትወስደው ዘንድ አትመለስ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ፥ ለመጻተኛና ለድሃ አደግ ለመበለትም ተወው። |
20. | የወይራህን ፍሬ ባረገፍህ ጊዜ ከቅርንጫፎቹ ላይ ማርገፉን ለማጣራት አትመለስ፤ ለመጻተኛና ለድሀ አደግ ለመበለትም ይሁን። |
21. | የወይንህን ፍሬ በቈረጥህ ጊዜ ቃርሚያውን አትልቀመው፤ ለመጻተኛና ለድሀ አደግ ለመበለትም ይሁን። |
22. | አንተም በግብፅ አገር ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ ስለዚህ ይህን ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ። |
← Deuteronomy (24/34) → |