← Deuteronomy (22/34) → |
1. | የወንድምህ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ብታይ ቸል አትበል፤ ወደ ወንድምህ መልሰው። |
2. | ወንድምህም በአቅራቢያህ ባይሆን ወይም ባታውቀው ይዘህ ወደ ቤትህ ትገባለህ፤ ወንድምህ እስኪሻው ድረስ በአንተ ዘንድ ይቀመጣል፥ ለእርሱም ትመልሰዋለህ። |
3. | እንዲህም በአህያው ወይም በልብሱ ታደርጋለህ፤ እንዲህም በወንድምህ በጠፋበት ነገር ሁሉ ባገኘኸው ጊዜ ታደርጋለህ፤ ቸል ልትለው አይገባህም። |
4. | የወንድምህ አህያ ወይም በሬው በመንገድ ወድቆ ብታይ ከእርሱ ጋር ሆነህ አነሣሣው እንጂ ቸል አትበለው። |
5. | ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፥ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፤ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና። |
6. | በመንገድ ስትሄድ በዛፍ ወይም በመሬት ላይ እናቲቱ በጫጩቶችዋ ወይም በእንቍላሎችዋ ላይ ተኝታ ሳለች የወፍ ጎጆ ብታገኝ፥ እናቲቱን ከጫጩቶዋ ጋር አትውሰድ። |
7. | ነገር ግን መልካም ይሆንልህ ዘንድ ዕድሜህም ይረዝም ዘንድ እናቲቱን ስደድ፥ ጫጩቶችንም ለአንተ ውሰድ። |
8. | አዲስ ቤት በሠራህ ጊዜ ማንም ከእርሱ ወድቆ ደሙን በቤትህ ላይ እንዳታመጣ በጣራው ዙሪያ መከታ አድርግለት። |
9. | የዘራኸው ዘርና ከወይኑ የወጣው አንድ ሆነው እንዳይጠፉብህ በወይንህ ቦታ ላይ ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ። |
10. | በበሬና በአህያ በአንድነት አትረስ። |
11. | ከተልባ እግርና ከበግ ጠጕር በአንድነት የተሠራ ልብስ አትልበስ። |
12. | በምትለብሰው በልብስህ በአራቱ ማዕዘን ዘርፍ አድርግ። |
13. | ማናቸውም ሰው ሚስት ቢያገባ፥ ከደረሰባትም በኋላ ቢጠላት፥ |
14. | የነውር ነገር አውርቶ። እኔ ይህችን ሴት ሚስት አድርጌ አገባኋት፥ በደርስሁባትም ጊዜ ድንግልናዋን አላገኘሁባትም ብሎ በክፉ ስም ቢያሳጣት፥ |
15. | የብላቴናይቱ አባትና እናት የድንግልናዋን ምልክት ወስደው በበሩ በአደባባይ ወደ ተቀመጡ ወደ ከተማ ሽማግሌዎች ያምጡት፤ |
16. | የብላቴናይቱም አባት ሽምግሌዎቹን። እኔ ለዚህ ሰው ልጄን ዳርሁለት እርሱም ጠላት፤ |
17. | እነሆም። በልጅህ ድንግልና አላገኘሁባትም ብሎ የነውር ነገር አወራባት፤ የልጄም ምልክት ይኸው ይላቸዋል። በከተማም ሽማግሌዎች ፊት ልብሱን ይዘረጋሉ። |
18. | የዚያችም ከተማ ሽማግሌዎች ያንን ሰው ወስደው ይግረፉት፤ |
19. | በእስራኤል ድንግል ላይ ክፉ ስም አምጥቶአልና መቶ የብር ሰቅል ያስከፍሉት፥ ለብላቴናይቱም አባት ይስጡት፤ እርስዋም ሚስት ትሁነው፥ በዕድሜውም ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይገባውም። |
20. | ነገሩ ግን እውነት ቢሆን፥ በብላቴናይቱም ድንግልናዋ ባይገኝ፥ |
21. | ብላቴናይቱን ወደ አባትዋ ቤት ደጅ ያውጡአት፥ በእስራኤልም ዘንድ የማይገባውን ነገር አድርጋለችና፥ በአባትዋም ቤት አመንዝራለችና የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩአት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ። |
22. | ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ፥ አመንዝራውና አመንዝራይቱ ሁለታቸው ይሙቱ፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከእስራኤል ታስወግዳለህ። |
23. | ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ልጃገረድ ቢያጭ፥ ሌላ ሰውም በከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእርስዋ ጋር ቢተኛ፥ |
24. | ሁለቱን ወደዚያች ከተማ በር አውጡአቸው፤ ብላቴናይቱ በከተማ ውስጥ ሳለች አልጮኸችምና፥ ሰውዮውም የባልንጀራውን ሚስት አስነውሮአልና እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሩአቸው፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ። |
25. | ነገር ግን ሰው የታጨችውን ልጃገረድ በሜዳ ቢያገኛት፥ በግድ አሸንፎም ቢደርስባት፥ ያ የደረሰባት ሰው ብቻውን ይገደል። |
26. | በብላቴናይቱ ላይ ግን ምንም አታድርጉ በብላቴናይቱ ላይ ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት የለባትም፤ ሰው በባልንጀራው ላይ ተነሥቶ እንደሚገድለው ይህ፤ ነገር ደግሞ እንደዚሁ ነውና፤ |
27. | በሜዳ ባገኛት ጊዜ የታጨችው ልጃገረድ ጮኻለችና፥ የሚታደጋትም አልነበረምና። |
28. | ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ያልታጨች ልጃገረድ ቢያገኝ፥ ወስዶም ቢደርስባት፥ ቢያገኙትም፥ |
29. | ያ የደረሰባት ሰው አምሳ የብር ሰቅል ለብላቴናይቱ አባት ይስጥ፤ አስነውሮአታልና ሚስት ትሁነው፤ በዕድሜውም ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይገባውም። |
30. | ማናቸውም ሰው የአባቱን ሚስት አይውሰድ፥ የአባቱንም ልብስ ጫፍ አይግለጥ። |
← Deuteronomy (22/34) → |