← Deuteronomy (2/34) → |
1. | እግዚአብሔርም እንዳለኝ ተመልሰን በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሄድን፤ የሴይርንም ተራራ ብዙ ቀን ዞርን። |
2. | እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረኝ። |
3. | ይህን ተራራ መዞር ይበቃችኋል፤ ተመልሳችሁ ወደ ሰሜን ሂዱ። |
4. | ሕዝቡንም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። በሴይር ላይ በተቀመጡት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ልጆች አገር ታልፋላችሁ፥ እነርሱም ይፈሩአችኋል፤ እንግዲህ እጅግ ተጠንቀቁ። |
5. | የሴይርን ተራራ ለዔሳው ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ እኔ ከምድራቸው የጫማ መርገጫ ታህል እንኳ አልሰጣችሁምና አትጣሉአቸው። |
6. | ከእነርሱ በገንዘብ ምግብ ገዝታችሁ ትበላላችሁ፤ ውኃም ደግሞ በገንዘብ ገዝታችሁ ትጠጣላችሁ። ብ ገዝታችሁ ትጠጣላችሁ። |
7. | አምላክህ እግዚአብሔር የእጅህን ሥራ ሁሉ ባርኮልሃልና፤ በዚህ በታላቅ ምድረ በዳ መሄድህን አውቆአል፤ በዚህ አርባ ዓመት ውስጥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነበረ፥ አንዳችም አላጣህም። |
8. | በሴይርም ከተቀመጡት ከወንድሞቻችን ከዔሳው ልጆች በዓረባ መንገድ ከኤላትና ከዔጽዮንጋብር አለፍን። ተመልሰንም በሞዓብ ምድረ በዳ መንገድ አለፍን። |
9. | እግዚአብሔርም አለኝ። እኔ ዔርን ለሎጥ ልጆች ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ ከምድሩ ርስት አልሰጣችሁምና ሞዓብን አትጣላ በሰልፍም አትውጋቸው። |
10. | አስቀድሞ ታላቅና ብዙ ሕዝብ እንደ ዔናቅም ልጆች በቁመት የረዘሙ ኤሚማውያን በዚያ ይቀመጡ ነበር። |
11. | እነርሱም ደግሞ እንደ ዔናቅ ልጆች ራፋይም ይባሉ ነበር፤ ሞዓባውያን ግን ኤሚም ይሉአቸዋል። |
12. | ሖራውያንም ደግሞ አስቀድሞ በሴይር ላይ ተቀምጠው ነበር፥ የዔሳው ልጆች ግን አሳደዱአቸው፤ እግዚአብሔርም በሰጠው በርስቱ ምድር እስራኤል እንዳደረገ፥ ከፊታቸው አጠፉአቸው፥ በስፍራቸውም ተቀመጡ። |
13. | እግዚአብሔርም። ተነሡ የዘሬድንም ፈፋ ተሻገሩ አለ። |
14. | የዘሬድንም ፈፋ ተሻገርን። የዘሬድንም ፈፋ እስከ ተሻገርንበት ድረስ፥ እግዚአብሔር እንደ ማለባቸው የሰልፈኞች ትውልድ ሁሉ ከሰፈሩ መካከል እስከ ጠፉ ድረስ፥ ከቃዴስ በርኔ የተጓዝንበት ዘመን ሠላሳ ስምንት ዓመት ሆነ። |
15. | ከሰፈርም መካከል ተቈርጠው እስኪጠፉ ድረስ የእግዚአብሔር እጅ በላያቸው ነበረ። |
16. | እንዲህም ሆነ፤ ሰልፈኞቹ ከጠፉ ከሕዝቡም መካከል ከሞቱ በኋላ፥ |
17. | እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረኝ። |
18. | አንተ ዛሬ የሞዓብን ዳርቻ ዔርን ታልፋለህ፤ |
19. | ለሎጥም ልጆች ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ ከአሞን ልጆች ምድር ርስት አልሰጥህምና በአሞን ልጆች አቅራቢያ ስትደርስ አትጣላቸው አትውጋቸውም። |
20. | ያም ደግሞ የራፋይም ምድር ተብሎ ተቆጠረ፤ ራፋይምም አስቀድሞ በዚያ ተቀምጠው ነበር፤ አሞናውያን ግን ዘምዙማውያን ብለው ይጠሩአቸዋል። |
21. | ታላቅና ብዙም ሕዝብ እንደ ዔናቅም ልጆች ቁመታቸው የረዘመ ነበሩ፤ እግዚአብሔር ከፊታቸው አጠፋቸው፤ እነርሱንም አሳድደው በስፍራቸው ተቀመጡ። |
22. | ሖራውያንን ከፊታቸው አጥፍቶ በሴይር ለተቀመጡት ለዔሳው ልጆች እንዳደረገ እንዲሁ ለእነርሱ አደረገ፤ እነርሱንም አሳድደው በስፍራቸው እስከ ዛሬ ድረስ ተቀመጡ። |
23. | እስከ ጋዛም ድረስ በመንደሮች ተቀምጠው የነበሩትን ኤዋውያንን ከከፍቶር የወጡ ከፍቶራውያን አጠፉአቸው፥ በስፍራቸውም ተቀመጡ። |
24. | ደግሞም አለ። ተነሥታችሁ ሂዱ፥ የአርኖንንም ሸለቆ ተሻገሩ፤ እነሆ፥ አሞራዊውን የሐሴቦንን ንጉሥ ሴዎንን ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ፤ እርስዋን በመውረስ ጀምር፥ ከእርሱም ጋር ተዋጋ። |
25. | ከሰማይ በታች ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ ማስደንገጥህንና ማስፈራትህን እሰድድ ዘንድ ዛሬ እጀምራለሁ፤ ወሬህን በሰሙ ጊዜ በፊትህ ይንቀጠቀጣሉ፥ ድንጋጤም ይይዛቸዋል። |
26. | ከቅዴሞትም ምድረ በዳ የሰላምን ቃል ይነግሩት ዘንድ ወደ ሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን እንዲህ ብዬ መልእክተኞችን ላክሁ። በአገርህ ላይ ልለፍ፤ |
27. | በአውራ ጎዳና እሄዳለሁ፥ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አልተላለፍም። |
29. | የምበላውን ምግብ በገንዘብ ሽጥልኝ፥ የምጠጣውንም ውኃ በገንዘብ ስጠኝ፤ በሴይር የተቀመጡ የዔሳው ልጆች በዔርም የተቀመጡ ሞዓባውያን እንዳደረጉልኝ፥ አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ምድር ዮርዳኖስን እስክሻገር ድረስ ብቻ በእግሬ ልለፍ። |
30. | የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን ግን ያሳልፈን ዘንድ አልፈቀደም፤ እንደ ዛሬው ሁሉ በእጅህ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መንፈሱን አደንድኖታልና፥ ልቡንም አጽንቶታልና። |
31. | እግዚአብሔርም። ሴዎንንና ምድሩን በእጅህ አሳልፌ መስጠት፥ እነሆ፥ ጀመርሁ፤ ምድሩን ትገዛት ዘንድ መውረስ ጀምር አለኝ። |
32. | ሴዎንም ሕዝቡም ሁሉ ሊጋጠሙን ወደ ያሀጽ ወጡ። |
33. | አምላካችንም እግዚአብሔር እርሱን አሳልፎ ሰጠን፤ እርሱንም ልጆቹንም ሕዝቡንም ሁሉ መታን። |
34. | በዚያን ጊዜም ከተሞቹን ሁሉ ወሰድን የተቀመጡባቸውንም ሰዎች ሁሉ ሴቶችንም ሕፃናቶችንም አጠፋን፤ አንዳችም አላስቀረንም፥ |
35. | ከብቶቻቸውንና ከከተሞቻቸው ያገኘነውን ብዝበዛ ለራሳችን ወሰድን እንጂ። |
36. | በአርኖን ቈላ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ከሸለቆውም ውስጥ ካለችው ከተማ ጀምረን እስከ ገለዓድ ድረስ ማናቸይቱም ከተማ አልጠነከረችብንም፤ አምላካችን እግዚአብሔር ሁሉን አሳልፎ ሰጠን። |
37. | ዳሩ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ወደ ከለከለን ሁሉ፥ ወደ አሞን ልጆች ምድር በያቦቅም ወንዝ አጠገብ ወዳለው ስፍራ ሁሉ በተራራማውም አገር ወዳሉት ከተሞች አልደረስንም። |
← Deuteronomy (2/34) → |