← Acts (23/28) → |
1. | ጳውሎስም ሸንጎውን ትኵር ብሎ ተመልክቶ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ አለ። |
2. | ሊቀ ካህናቱም ሐናንያ አፉን ይመቱት ዘንድ በአጠገቡ ቆመው የነበሩትን አዘዘ። |
3. | በዚያን ጊዜ ጳውሎስ። አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ፥ እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን? አለው። |
4. | በአጠገቡ የቆሙትም። የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን? አሉት። |
5. | ጳውሎስም። ወንድሞች ሆይ፥ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባላውቅ ነው፤ በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር ተብሎ ተጽፎአልና አላቸው። |
6. | ጳውሎስ ግን እኵሌቶቹ ሰዱቃውያን እኵሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል ብሎ በሸንጎው ጮኸ። |
7. | ይህንም ባለ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጥል ሆነ ሸንጎውም ተለያየ። |
8. | ሰዱቃውያን። ትንሣኤም መልአክም መንፈስም የለም የሚሉ ናቸውና፤ ፈሪሳውያን ግን ሁለቱን ያምናሉ። |
9. | ታላቅ ጩኸትም ሆነ፥ ከፈሪሳውያንም ወገን የሆኑት ጻፎች ተነሥተው። በዚህ ሰው ላይ ምንም ክፉ ነገር አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይስ መልአክ ተናግሮት ይሆን? ብለው ተከራከሩ። |
10. | ብዙ ጥልም በሆነ ጊዜ የሻለቃው ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ጭፍሮቹ ወርደው ከመካከላቸው እንዲነጥቁት ወደ ሰፈሩም እንዲያገቡት አዘዘ። |
11. | በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ። ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ አለው። |
12. | በጠባም ጊዜ አይሁድ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ በመሐላ ተስማሙ። |
13. | ይህንም ሴራ ያደረጉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር፤ |
14. | እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎቹ መጥተው። ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ ምንም እንዳንቀምስ ተረጋግመን ተማምለናል። |
15. | እንግዲህ አሁን እናንተ ከሸንጎው ጋር ሆናችሁ ስለ እርሱ አጥብቃችሁ እንደምትመረምሩ መስላችሁ ወደ እናንተ እንዲያወርደው ለሻለቃው አመልክቱት፤ እኛም ሳይቀርብ እንድንገድለው የተዘጋጀን ነን አሉአቸው። |
16. | የጳውሎስ የእኅቱ ልጅ ግን ደባቸውን በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ ወደ ሰፈሩ ገባና ለጳውሎስ ነገረው። |
17. | ጳውሎስም ከመቶ አለቆች አንዱን ጠርቶ። ይህን ብላቴና ወደ ሻለቃው ውሰድ፥ የሚያወራለት ነገር አለውና አለው። |
18. | እርሱም ይዞት ወደ ሻለቃው ወሰደውና። ይህ ብላቴና የሚነግርህ ነገር ስላለው እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶ ወደ አንተ እንድወስደው ለመነኝ አለው። |
19. | የሻለቃውም እጁን ይዞ ፈቀቅ አለና ለብቻው ሆኖ። የምታወራልኝ ነገር ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀው። |
20. | እርሱም። አይሁድ ስለ ጳውሎስ ከፊት ይልቅ አጥብቀህ እንደምትመረምር መስለህ፥ ነገ ወደ ሸንጎ ታወርደው ዘንድ ሊለምኑህ ተስማምተዋል። |
21. | እንግዲህ አንተ በጅ አትበላቸው፤ እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ ተማምለው ከእነርሱ ከአርባ የሚበዙ ሰዎች ያደቡበታልና፤ አሁንም የተዘጋጁ ናቸው የአንተንም ምላሽ ይጠብቃሉ አለው። |
22. | የሻለቃውም። ይህን ነገር ለእኔ ማመልከትህን ለማንም እንዳትገልጥ ብሎ ካዘዘ በኋላ ብላቴናውን አሰናበተው። |
23. | ከመቶ አለቆቹም ሁለት ጠርቶ። ወደ ቂሣርያ ይሄዱ ዘንድ ሁለት መቶ ወታደሮችንና ሰባ ፈረሰኞችን ሁለት መቶም ባለ ጦር መሣሪያዎችን ከሌሊቱ በሦስተኛው ሰዓት አዘጋጁ አላቸው። |
24. | ጳውሎስንም ወደ አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ በደኅና እንዲያደርሱት የሚያስቀምጡበትን ከብት ያዘጋጁ ዘንድ አዘዛቸው። |
25. | ደብዳቤም ጻፈ እንዲህ የሚል። |
26. | ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ ወደ ክቡር አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን። |
27. | ይህን ሰው አይሁድ ይዘው ሊገድሉት ባሰቡ ጊዜ ከጭፍሮቹ ጋር ደርሼ አዳንሁት፥ ሮማዊ እንደ ሆነ አውቄ ነበርና። |
28. | የሚከሰስበትንም ምክንያት አውቅ ዘንድ አስቤ ወደ ሸንጎአቸው አወረድሁት፤ |
29. | በሕጋቸውም ስለ መከራከር እንደ ከሰሱት አገኘሁ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያደርስ ክስ አይደለም። |
30. | በዚህም ሰው አይሁድ ሴራ እንዲያደርጉበት ባመለከቱኝ ጊዜ ያን ጊዜውን ወደ አንተ ሰደድሁት፥ ከሳሾቹንም ደግሞ በፊትህ ይከሱት ዘንድ አዘዝኋቸው። ደኅና ሁን። |
31. | ወታደሮቹም እንደ ታዘዙት ጳውሎስን ይዘው በሌሊት ወደ አንቲጳጥሪስ አደረሱት፤ |
32. | በነገውም ከእርሱ ጋር ይሄዱ ዘንድ ፈረሰኞችን ትተው ወደ ሰፈር ተመለሱ። |
33. | እነዚያም ወደ ቂሣርያ ገብተው ደብዳቤውን ለአገረ ገዡ በሰጡ ጊዜ ጳውሎስን ደግሞ በፊቱ አቆሙት። |
34. | ካነበበውም በኋላ የወዴት አውራጃ እንደ ሆነ ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑንም ባወቀ ጊዜ። |
35. | ከሳሾችህ ደግሞ ሲመጡ እሰማሃለሁ አለው፤ በሄሮድስም ግቢ ውስጥ ይጠብቁት ዘንድ አዘዘ። |
← Acts (23/28) → |