← 2Samuel (6/24) → |
1. | ዳዊትም ዳግም ከእስራኤል የተመረጡትን ሠላሳ ሺህ ያህል ሰው ሰበሰበ። |
2. | ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ በይሁዳ ካለች ከበኣል ተነሥተው በኪሩቤል ላይ በተቀመጠ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያመጡ ዘንድ ሄዱ። |
3. | የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑ፥ በኮረብታውም ላይ ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት አመጡት፤ የአሚናዳብ ልጆችም ዖዛ እና አሒዮ አዲሱን ሰረገላ ይነዱ ነበር። |
4. | በኮረብታውም ላይ ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት የእግዚአብሔርን ታቦት ባመጡ ጊዜ አሒዮ በታቦቱ ፊት ይሄድ ነበር። |
5. | ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር። |
6. | ወደ ናኮንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦት ያዘ። |
7. | የእግዚአብሔርም ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ድፍረቱ በዚያው ቀሠፈው፤ በእግዚአብሔርም ታቦት አጠገብ በዚያው ሞተ። |
8. | እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ሰበረው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያ ስፍራ ስም የዖዛ ስብራት ተብሎ ተጠራ። |
9. | በዚያም ቀን ዳዊት እግዚአብሔርን ፈራና። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል? አለ። |
10. | ዳዊትም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ ያመጣው ዘንድ አልወደደም፤ ዳዊትም በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት አገባው። |
11. | የእግዚአብሔርም ታቦት በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ያህል ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤቱን ሁሉ ባረከ። |
12. | ንጉሡ ዳዊትም እግዚአብሔር የአቢዳራን ቤትና የነበረውን ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ታቦት እንደ ባረከ ሰማ። ዳዊትም ሄዶ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በደስታ አመጣው። |
13. | የእግዚአብሔርንም ታቦት የተሸከሙ ስድስት እርምጃ በሄዱ ጊዜ አንድ በሬና አንድ ፍሪዳ ሠዋ። |
14. | ዳዊትም በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ፊት ይዘፍን ነበር፤ ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ለብሶ ነበር። |
15. | ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከትም እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡ። |
16. | የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በገባ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፥ ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘፍን አየች፤ በልብዋም ናቀችው። |
17. | የእግዚአብሔርንም ታቦት አገቡ፥ ዳዊትም በተከለለት ድንኳን ውስጥ በስፍራው አኖሩት፤ ዳዊትም የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕትን በእግዚአብሔር ፊት አሳረገ። |
18. | ዳዊትም የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት ማሳረግ ከፈጸመ በኋላ ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም መረቀ። |
19. | ለሕዝቡም ሁሉ ለእስራኤል ወገን ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ አንዳንድም የሥጋ ቍራጭ አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ። ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ቤቱ ሄደ። |
20. | ዳዊትም ቤተ ሰቡን ሊመርቅ ተመለሰ። የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ለመቀበል ወጣችና። ምናምንቴዎች እርቃናቸውን እንደሚገልጡ የእስራኤል ንጉሥ በባሪያዎቹ ቈነጃጅት ፊት እርቃኑን በመግለጡ ምንኛ የተከበረ ነው! አለችው። |
21. | ዳዊትም ሜልኮልን። በእግዚአብሔር ፊት ዘፍኛለሁ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ። |
22. | አሁንም ከሆንሁት ይልቅ የተናቅሁ እሆናለሁ፥ በዓይንሽም እዋረዳለሁ፤ ነገር ግን በተናገርሽው ቈነጃጅት ዘንድ እከብራለሁ አላት። |
23. | የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም።፤ |
← 2Samuel (6/24) → |