← 2Samuel (21/24) → |
1. | በዳዊትም ዘመን ሦስት ዓመት ያህል ቀጥሎ ራብ ሆነ፤ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ፊት ጠየቀ። እግዚአብሔርም። የገባዖንን ሰዎች ስለ ገደለ በሳኦልና በቤቱ ላይ ደም አለበት አለ። |
2. | ንጉሡም የገባዖንን ሰዎች ጠራ፤ የገባዖን ሰዎችም ከአሞራውያን የተረፉ ነበሩ እንጂ ከእስራኤል ልጆች ወገን አልነበሩም፤ የእስራኤልም ልጆች ምለውላቸው ነበር፤ ሳኦል ግን ለእስራኤል ልጆችና ለይሁዳ ስለ ቀና ሊገድላቸው ወድዶ ነበር። |
3. | ዳዊትም የገባዖንን ሰዎች። የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ምን ላድርግላችሁ? ማስተስረያውስ ምንድር ነው? አላቸው። |
4. | የገባዖን ሰዎችም። በእኛና በሳኦል ወይም በእኛና በቤቱ መካከል ያለው የብርና የወርቅ ነገር አይደለም፤ ከእስራኤልም ወገን እኛ የምንገድለው የለም አሉት። እርሱም። የምትናገሩትን አደርግላችኋለሁ አለ። |
5. | ንጉሡንም። እኛን ካጠፋ፥ በእስራኤልም ዳርቻ ሁሉ እንዳንቀመጥ መፍረሳችንን |
6. | ካሰበው ሰው ልጆች ሰባት ሰዎች አሳልፈህ ስጠንና ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ ለእግዚአብሔር እንሰቅላቸዋለን አሉት። ንጉሡም። እሰጣችኋለሁ አለ። |
7. | ንጉሡም በሳኦል ልጅ በዮናታንና በዳዊት መካከል ስለ ነበረው ስለ እግዚአብሔር መሐላ የሳኦልን ልጅ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን አዳነ። |
8. | ንጉሡም ለሳኦል የወለደቻቸውን የኢዮሄል ልጅ የሪጽፋን ሁለቱን ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን ለመሓላታዊውም ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደቻቸውን የሳኦልን ልጅ የሜሮብን አምስቱን ልጆች ወሰደ፥ |
9. | ለገባዖንም ሰዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት በተራራው ላይ ሰቀሉአቸው፥ ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፤ እህል በሚታጨድበት ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ተገደሉ። |
10. | የኢዮሄልም ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ ከመከር ወራት ጀምሮ ዝናብ ከሰማይ እስኪዘንብ ድረስ በድንጋይ ላይ ዘረጋችው፤ በቀንም ወፎች በሌሊትም አራዊት ያርፉባቸው ዘንድ አልተወችም። |
11. | የሳኦልም ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ለዳዊት ነገሩት። |
12. | ዳዊትም ሄደ፥ ሳኦልንም በጊልቦዓ በገደሉ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤትሳን አደባባይ ከሰረቁት ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ፤ |
13. | ከዚያም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ይዞ መጣ፤ የተሰቀሉትንም ሰዎች አጥንት ሰበሰቡ። |
14. | የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት በብንያም አገር በጼላ በአባቱ በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡም ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ስለ አገሩ የተለመነውን ሰማ። |
15. | በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤልም መካከል ደግሞ ሰልፍ ነበረ፤ ዳዊትም ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹ ወረዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ተዋጉ፤ ዳዊትም ደከመ። |
16. | ከራፋይም ወገን የነበረው ይሽቢብኖብ ዳዊትን ይገድል ዘንድ አሰበ፤ የጦሩም ሚዛን ክብደት ሦስት መቶ ሰቅል ናስ ነበረ፥ አዲስም የጦር መሣሪያ ታጥቆ ነበር። |
17. | የጽሩያም ልጅ አቢሳ አዳነው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለው። ያንጊዜም የዳዊት ሰዎች። አንተ የእስራኤልን መብራት እንዳታጠፋ ከእንግዲህ ወዲህ ከእኛ ጋር ለሰልፍ አትወጣም ብለው ማሉለት። |
18. | ከዚህም በኋላ እንደ ገና በጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ሆነ፥ ኩሳታዊውም ሴቦካይ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሳፍን ገደለ። |
19. | ደግሞም በጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ነበረ፤ የቤተ ልሔማዊውም የየዓሬኦርጊም ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጌት ሰው ጎልያድን ገደለ። |
20. | ደግሞም በጌት ላይ ሰልፍ ሆነ፤ በዚያም በእጁና በእግሩ ስድስት ስድስት ሁላሁሉ ሀያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ረጅም ሰው ነበረ፤ እርሱ ደግሞ ከራፋይም የተወለደ ነበረ። |
21. | እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሣማ ልጅ ዮናታን ገደለው። |
22. | እነዚያም አራቱ በጌት ውስጥ ከራፋይም የተወለዱ ነበሩ፤ በዳዊትም እጅ በባሪያዎቹም እጅ ወደቁ። |
← 2Samuel (21/24) → |