← 2Samuel (2/24) → |
1. | ከዚያም በኋላ ዳዊት። ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም። ውጣ አለው። ዳዊትም። ወዴት ልውጣ? አለ። እርሱም። ወደ ኬብሮን ውጣ አለው። |
2. | ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ ጋር ወደዚያ ወጣ። |
3. | ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎችና ቤተ ሰባቸውን ሁሉ አመጣ፤ በኬብሮንም ከተሞች ተቀመጡ። |
4. | የይሁዳም ሰዎች መጥተው በይሁዳ ቤት ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን በዚያ ቀቡት። ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ናቸው ብለው ለዳዊት ነገሩት። |
5. | ዳዊትም ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው። እናንተ ለጌታችሁ ለሳኦል ይህን ቸርነት አድርጋችኋልና፥ ቀብራችሁትማልና በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ሁኑ። |
6. | አሁንም እግዚአብሔር ቸርነትንና እውነትን ያድርግላችሁ፤ ይህንም ነገር አድርጋችኋልና እኔ ደግሞ ይህን ቸርነት እመልስላችኋለሁ። |
7. | አሁንም ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአልና እጃችሁ ትጽና፥ እናንተም ጨክኑ፤ ዳግም የይሁዳ ቤት በእነርሱ ላይ ንጉሥ እሆን ዘንድ ቀብተውኛል። |
8. | የሳኦልም ጭፍራ አለቃ የኔር ልጅ አበኔር የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደመሃናይም አሻገረው፤ |
9. | በገለዓድና በአሹራውያን በኢይዝራኤልም በኤፍሬምም በብንያምም በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሠው። |
10. | የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴም በእስራኤል ላይ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ነገሠ፤ ነገር ግን የይሁዳ ቤት ዳዊትን ተከተለ። |
11. | ዳዊትም በይሁዳ ቤት ነግሦ በኬብሮን የተቀመጠበት ዘመን ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ። |
12. | የኔር ልጅ አበኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ባሪያዎች ከመሃናይም ወደ ገባዖን ወጡ። |
13. | የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ባሪያዎች ወጥተው በገባዖን ውኃ መቆሚያ አጠገብ ተገናኙአቸው፤ በውኃውም መቆሚያ በአንዱ ወገን እነዚህ፥ በሌላውም ወገን እነዚያ ሆነው ተቀመጡ። |
14. | አበኔርም ኢዮአብን። ጕልማሶች ይነሡ፥ በፊታችንም ይቈራቈሱ አለው፤ ኢዮአብም። ይነሡ አለ። |
15. | ለብንያም ወገንና ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ አስራ ሁለት፥ ከዳዊትም ባሪያዎች አሥራ ሁለት ተቈጥረው ተነሡ። |
16. | ሁሉም እያንዳንዱ የወደረኛውን ራስ ያዘ፥ ሰይፉንም በወደረኛው ጎን ሻጠ፥ ተያይዘውም ወደቁ። የዚያም ስፍራ ስም የስለታም ሰይፍ እርሻ ተብሎ ተጠራ፥ እርሱም በገባዖን ነው። |
17. | በዚያም ቀን ጽኑ ሰልፍ ሆነ፤ በዳዊትም ባሪያዎች ፊት አበኔርና የእስራኤል ሰዎች ተሸነፉ። |
18. | በዚያም ሦስቱ የጽሩያ ልጆች ኢዮአብና አቢሳ አሣሄልም ነበሩ፤ አሣሄልም እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ። |
19. | አሣሄልም የአበኔርን ፍለጋ ተከታተለ፥ አበኔርንም ከማሳደድ ቀኝና ግራ አላለም። |
20. | አበኔርም ዘወር ብሎ ተመለከተና። አንተ አሣሄል ነህን? አለ። እርሱም። እኔ ነኝ አለ። |
21. | አበኔርም። ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ በል፤ አንድ ጕልማሳ ያዝ፥ መሣርያውንም ውሰድ አለው። አሣሄል ግን እርሱን ከማሳደድ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ። |
22. | አበኔርም አሣሄልን። ከምድር ጋር እንዳላጣብቅህ እኔን ከማሳደድ ፈቀቅ በል፤ ወደ ወንድምህ ወደ ኢዮአብ ፊቴን አቅኝቼ አይ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል? አለው። |
23. | ነገር ግን ከእርሱ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ፤ አበኔርም በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፥ ጦሩም በኋላው ወጣ፥ በዚያም ስፍራ ወድቆ ሞተ። አሣሄልም ወድቆ በሞተበቱ ስፍራ የሚያልፍ ሁሉ ይቆም ነበር። |
24. | ኢዮአብና አቢሳም አበኔርን አሳደዱ፤ በገባዖንም ምድረ በዳ መንገድ በጋይ ፊት ለፊት እስካለው እስከ አማ ኮረብታ ድረስ በወጡ ጊዜ ፀሐይ ጠለቀች። |
25. | የብንያምም ልጆች ወደ አበኔር ተሰበሰቡ፥ በአንድነትም ሆኑ፥ በኮረብታም ራስ ላይ ቆሙ። |
26. | አበኔርም ወደ ኢዮአብ ጮኸ። ሰይፍ በውኑ እስከ ዘላለም ያጠፋልን? ፍጻሜውሳ መራራ እንደ ሆነ አታውቅምን? ሕዝቡ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ ይመለሱ ዘንድ ሕዝቡን የማትናገር እስከ መቼ ነው? አለው። |
27. | ኢዮአብም። ሕያው እግዚአብሔርን! ባትናገር ኖሮ ሕዝቡ በጥዋት ወጥተው በሄዱ ነበር፥ ወንድሞቻቸውንም ማሳደድ በተዉ ነበር አለ። |
28. | ኢዮአብም ቀንደ መለከት ነፋ፥ ሕዝቡም ሁሉ ቆመ፥ ከዚያም በኋላ እስራኤልን አላሳደደም፥ ሰልፍም አላደረገም። |
29. | አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ዓረባ እያለፉ ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፥ ቢትሮንንም ሁሉ ካለፉ በኋላ ወደ መሃናይም መጡ። |
30. | ኢዮአብም አበኔርን ከማሳደድ ተመለሰ፤ ሕዝቡንም ሁሉ ሰበሰበ፥ ከዳዊትም ባሪያዎች ከአሣሄል ሌላ አሥራ ዘጠኝ ሰዎች ጐደሉ። |
31. | የዳዊትም ባሪያዎች ከብንያምና ከአበኔር ሰዎች ሦስት መቶ ስድሳ ያህል ገደሉ። |
32. | አሣሄልንም አንሥተው በቤተ ልሔም በአባቱ መቃብር ቀበሩት፤ ኢዮአብና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ፥ በኬብሮንም አነጉ። |
← 2Samuel (2/24) → |