← 2Kings (25/25) |
1. | ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠኝኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ በዙሪያዋም ዕርድ ሠሩባት። |
2. | ከተማይቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ እስከ አሥራ አንደኛው ዓመት ድረስ ተከብባ ነበር። |
3. | በአራተኛውም ወር በዘጠኝኛው ቀን በከተማይቱ ራብ ጸንቶ ነበርና ለአገሩ ሰዎች እንጀራ ታጣ። |
4. | ከተማይቱም ተሰበረች፥ ሰልፈኞችም ሁሉ በሁለት ቅጥር መካከል ባለው በር ወደ ንጉሡ አትክልት በሚወስደው መንገድ በሌሊት ሸሹ፤ ከለዳውያንም በከተማይቱ ዙሪያ ነበሩ፤ በዓረባም መንገድ ሄዱ። |
5. | የከለዳውያንም ሠራዊት ንጉሡን ተከታተሉ፥ በኢያሪኮም ሜዳ ያዙት፤ ሠራዊቱም ሁሉ ከእርሱ ተለይተው ተበትነው ነበር። |
6. | ንጉሡንም ይዘው የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጡት፤ ፍርድም ፈረዱበት። |
7. | የሴዴቅያስንም ልጆች በፊቱ ገደሉአቸው፤ የሴዴቅያስንም ዓይኖች አወጡ፥ በሰንሰለትም አሰሩት፥ ወደ ባቢሎንም ወሰዱት። |
8. | በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር በአሥራ ዘጠኝኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ባሪያ የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። |
9. | የእግዚአብሔርንም ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ፤ የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ፥ ታላላቆቹን ቤቶች ሁሉ፥ በእሳት አቃጠለ። |
10. | ከዘበኞቹም አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት ሁሉ የኢየሩሳሌምን ቅጥር ዙሪያዋን አፈረሱ። |
11. | የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ ውስጥ የቀረውን ሕዝብ፥ ሸሽተውም ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን፥ የቀሩትንም ሕዝብ አፈለሰ። |
12. | የዘበኞቹም አለቃ ከአገሩ ድሆች ወይን ተካዮችና አራሾች እንዲሆኑ አስቀረ። |
13. | ከለዳውያንም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የነበሩትን የናስ ዓምዶች፥ በእግዚአብሔርም ቤት የነበሩትን መቀመጫዎችና የናስ ኵሬ ሰባበሩ፥ ናሱንም ወደ ባቢሎን ወሰዱ። |
14. | ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹንም መኰስተሪያዎቹንና ጭልፋዎቹንም የሚያገለግሉበትንም የናስ ዕቃ ሁሉ ወሰዱ። |
15. | የዘበኞቹም አለቃ ማንደጃዎቹንና መቀመጨዎቹን፥ የወርቁን ዕቃ ሁሉ በወርቅ፥ የብሩንም በብር አድርጎ ወሰደ። |
16. | ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ቤት የሠራቸውን ሁለቱን ዓምዶች አንዱንም ኵሬ መቀመጫዎቹንም ወሰደ፤ ለእነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ናስ ሚዛን አልነበረውም። |
17. | የአንዱም ዓምድ ቁመት አሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የናስም ጕልላት ነበረበት፤ የጕልላቱም ርዝመት ሦስት ክንድ ነበረ፥ በጕልላቱም ላይ በዙሪያው የናስ መርበብና ሮማኖች ነበሩ፤ እንዲሁም ደግሞ በሁለተኛው ዓምድ ላይ መርበብ ነበረበት። |
18. | የዘበኞቹም አለቃ ታላቁን ካህን ሠራያን ሁለተኛውንም ካህን ሶፎንያስን ሦስቱንም በረኞች ወሰደ። |
19. | ከከተማይቱም በሰልፈኞች ላይ ተሾመው ከነበሩት አንዱን ጃንደረባ፥ በከተማይቱም የተገኙትን በንጉሡ ፊት የሚቆሙትን አምስቱን ሰዎች፥ የአገሩንም ሕዝብ የሚያሰልፍ የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ፥ በከተማይቱም ከተገኙት ከአገሩ ሕዝብ ስድሳ ሰዎች ወሰደ። |
20. | የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ወስዶ የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጣቸው። |
21. | የባቢሎንም ንጉሥ መታቸው፥ በሐማትም ምድር ባለችው በሪብላ ገደላቸው። እንዲሁ ይሁዳ ከአገሩ ተማረከ። |
22. | የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ምድር በቀረው ሕዝብ ላይ የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን አለቃ አደረገው። |
23. | የጭፍሮቹም አለቆች ሁሉ፥ የናታንያ ልጅ እስማኤል፥ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፥ የነጦፋዊውም የተንሑሜት ልጅ ሠራያ፥ የማዕካታዊውም ልጅ ያእዛንያ፥ ሰዎቻቸውም የባቢሎን ንጉሥ ጎዶልያስን እንደ ሾመ በሰሙ ጊዜ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጡ። |
24. | ጎዶልያስም። ከከለዳውያን ሎሌዎች የተነሣ አትፍሩ፥ በአገሩ ተቀመጡ፥ ለባቢሎንም ንጉሥ ተገዙ፥ መልካምም ይሆንላችኋል ብሎ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው ማለላቸው። |
25. | በሰባተኛው ወር ግን የመንግሥት ዘር የነበረ የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር አሥር ሰዎች መጥተው ጎዶልያስንና ከእርሱ ጋር በምጽጳ የነበሩትን አይሁድንና ከለዳውያንን እስኪሞቱ ድረስ መቱአቸው። |
26. | ከለዳውያንንም ፈርተው ነበርና ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡ ሁሉ የጭፍሮቹም አለቆች ተነሥተው ወደ ግብጽ መጡ። |
27. | እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማከረ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ዮርማሮዴቅ በነገሠ በአንደኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪንን ከወህኒ አወጣው፤ |
28. | በፍቅርም ተናገረው፥ ዙፋኑንም ከእርሱ ጋር በባቢሎን ከነበሩት ነገሥታት ዙፋን በላይ አደረገለት። |
29. | በወህኒም ውስጥ ለብሶት የነበረውን ልብስ ለወጠለት፤ ዮአኪንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ በፊቱ ሁልጊዜ እንጀራ ይበላ ነበር። |
30. | ንጉሡም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ የዘወትር ቀለብ ዕለት ዕለት ይሰጠው ነበር። |
← 2Kings (25/25) |