← 2Kings (13/25) → |
1. | በይሁዳ ንጉሥ በአካዝያስ ልጅ በኢዮአስ በሀያ ሦስተኛው ዓመት የኢዩ ልጅ ኢዮአካዝ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ አሥራ ሰባትም ዓመት ነገሠ። |
2. | በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፥ እስራኤልንም ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኃጢአት ተከተለ፤ ከእርስዋም አልራቀም። |
3. | የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በዘመኑም ሁሉ በሶርያው ንጉሥ በአዛሄል እጅ፥ በአዛሄልም ልጅ በወልደ አዴር እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር። |
4. | ኢዮአካዝም እግዚአብሔርን ለመነ፤ እግዚአብሔርም የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን ያስጨነቀበትን ጭንቀት አይቶአልና ሰማው። |
5. | እግዚአብሔርም ለእስራኤል ታዳጊ ሰጠ፥ ከሶርያውያንም እጅ ዳኑ፤ የእስራኤልም ልጆች እንደ ቀድሞው ጊዜ በድንኳናቸው ተቀመጡ። |
6. | ነገር ግን በእርስዋ ሄዱ እንጂ እስራኤልን ካሳተው ከኢዮርብዓም ቤት ኃጢአት አልራቁም፤ ደግሞም የማምለኪያ ዐፀድ በሰማርያ ቆሞ ቀረ። |
7. | ለኢዮአካዝም ከአምሳ ፈረሰኞች፥ ከአሥርም ሰረገሎች፥ ከአሥር ሺህም እግረኞች በቀር ሕዝብ አልቀረለትም፤ የሶርያ ንጉሥ አጥፍቶአቸዋልና፥ በአውድማም እንዳላ ዕብቅ አድቅቆአቸዋልና። |
8. | የቀረውም የኢዮአካዝ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጭከናውም፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? |
9. | ኢዮአካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት፤ ልጁም ዮአስ በፋንታው ነገሠ። |
10. | በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ አሥራ ስድስትም ዓመት ነገሠ። |
11. | በእግዚአብሔር ፊት ክፋ ነገር አደረገ፤ እስራኤልን በሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት ሁሉ ሄደ እንጂ ከእርስዋ አልራቀም። |
12. | የቀረውም የዮአስ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ከይሁዳም ከአሜስያስ ጋር የተዋጋበት ጭከና፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? |
13. | ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ ኢዮርብዓምም በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ዮአስም በሰማርያ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ። |
14. | ኤልሳዕም በሚሞትበት በሽታ ታመመ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ወደ እርሱ ወርዶ በፊቱ አለቀሰና። አባቴ ሆይ፥ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች አለ። |
15. | ኤልሳዕም። ቀስትና ፍላጻዎች ውሰድ አለው፤ ቀስቱንና ፍላጻዎችንም ወሰደ። |
16. | የእስራኤልንም ንጉሥ። እጅህን በቀስቱ ላይ ጫን አለው። እጁንም ጫነበት፤ ኤልሳዕም እጁን በንጉሡ እጅ ላይ ጭኖ። |
17. | የምስራቁን መስኮት ክፈት አለ፤ ከፈተውም። ኤልሳዕም። ወርውር አለ፤ ወረወረውም። እርሱም። የእግዚአብሔር መድኃኒት ፍላጻ ነው፤ በሶርያ ላይ የመድኃኒት ፍላጻ ነው፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ሶርያዊያንን በአፌቅ ትመታለህ አለ። |
18. | ደግሞም። ፍላጻዎቹን ውሰድ አለው፤ ወሰዳቸውም። የእስራኤልንም ንጉሥ። ምድሩን ምታው አለው። ሦስት ጊዜም መትቶ ቆመ። |
19. | የእግዚአብሔርም ሰው ተቆጥቶ። አምስት ወይም ስድስት ጊዜ መትተኸው ኖሮ ሶርያን እስክታጠፋው ድረስ በመታኸው ነበር፤ አሁን ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ሶርያን ትመታለህ አለ። |
20. | ኤልሳዕም ሞተ፥ ቀበሩትም። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር። |
21. | ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋ ጣዮችን አዩ፥ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት፤ የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዮው ድኖ በእግሩ ቆመ። |
22. | የሶርያም ንጉሥ አዛሄል በኢዮአካዝ ዘመን ሁሉ እስራኤልን አስጨነቀ፤ |
23. | እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፥ ማራቸውም፥ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ስላደረገውም ቃል ኪዳን እነርሱን ተመለከተ፤ ሊያጠፋቸውም አልወደደም፥ ፈጽሞም ከፊቱ አልጣላቸውም። |
24. | የሶርያም ንጉሥ አዛሄል ሞተ፤ ልጁም ወልደ አዴር በፋንታው ነገሠ። |
25. | አዛሄልም ከአባቱ ከኢዮአካዝ እጅ በሰልፍ የወሰዳቸውን ከተሞች የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከአዛሄል ልጅ ከወልደ አዴር እጅ ወሰደ። ዮአስም ሦስት ጊዜ መታው፥ የእስራኤልንም ከተሞች መለሰ። |
← 2Kings (13/25) → |