← 2Kings (10/25) → |
1. | ለአክዓብም በሰማርያ ሰባ ልጆች ነበሩት፤ ኢዩም ደብዳቤ ጻፈ፤ የአክዓብን ልጆች ለሚያሳድጉ ለሰማርያ ታላላቆችና ሽማግሌዎች። |
2. | ይህ ደብዳቤ አሁን በደረሳችሁ ጊዜ የጌታችሁ ልጆች ሰረገሎችና ፈረሶችም የተመሸገችም ከተማ መሣሪያዎችም በእናንተ ዘንድ አሉና፥ |
3. | ከጌታችሁ ልጆች ደስ የሚያሰኛችሁንና የሚሻላችሁን ምረጡ፥ በአባቱም ዙፋን አስቀምጡት፥ ስለ ጌታችሁም ቤት ተዋጉ ብሎ ወደ ሰማርያ ሰደደ፤ |
4. | እነርሱ ግን እጅግ ፈርተው። እነሆ፥ ሁለቱ ነገሥታት በፊቱ ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም፤ እኛስ እንዴት እንቆማለን? አሉ። |
5. | የቤቱ አለቃ፥ የከተማይቱም አለቃ፥ ሽማግሌዎችና ልጆቹን የሚያሳድጉ። እኛ ባሪያዎችህ ነን፥ ያዘዝኸንም ሁሉ እናደርጋለን፤ ንጉሥም በላያችን አናነግሥም፤ የምትወድደውን አድርግ ብለው ወደ ኢዩ ላኩ። |
6. | ሁለተኛም። ወገኖቼስ እንደ ሆናችሁ፥ ነገሬንም ከሰማችሁ፥ የጌታችሁን ልጆች ራስ ቍረጡ፥ ነገም በዚህ ሰዓት ወደ ኢይዝራኤል ወደ እኔ ይዛችሁ ኑ ብሎ ደብዳቤ ጻፈላቸው። የንጉሡም ልጆች ሰባው ሰዎች በሚያሳድጓቸው በከተማይቱ ታላላቆች ዘንድ ነበሩ። |
7. | ደብዳቤውም በደረሳቸው ጊዜ የንጉሡን ልጆች ሰባውን ሰዎች ይዘው ገደሉአቸው፤ ራሳቸውንም በቅርጫት አድርገው ወደ እርሱ ወደ ኢይዝራኤል ላኩ። |
8. | መልእክተኛም መጥቶ። የንጉሡን ልጆች ራስ ይዘው መጥተዋል ብሎ ነገረው። እርሱም። እስከ ነገ ድረስ በበሩ አደባባይ ሁለት ክምር አድርጋችሁ አኑሩአቸው አለ። |
9. | በነጋውም ወጥቶ ቆመ፥ ሕዝቡንም ሁሉ። እናንተ ንጹሐን ናችሁ፤ እነሆ፥ ጌታዬን የወነጀልሁ የገደልሁትም እኔ ነኝ፤ እነዚህንስ ሁሉ የገደለ ማን ነው? |
10. | እግዚአብሔር በአክዓብ ቤት ላይ ከተናገረው ከእግዚአብሔር ቃል በምድር ላይ አንዳች እንዳይወድቅ አሁን እወቁ፤ እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ የተናገረውን አድርጎአል አላቸው። |
11. | ኢዩም ከአክዓብ ቤት የቀረውን ሁሉ፥ ታላላቆቹንም ሁሉ፥ ወዳጆቹንና ካህናቱን ማንም ሳይቀር በኢይዝራኤል ገደላቸው። |
12. | ተነሥቶም ወደ ሰማርያ ሄደ፤ በመንገድም ወዳለው ወደ በግ ጠባቂዎች ቤት በደረሰ ጊዜ፥ |
13. | ኢዩ ከይሁዳ ንጉሥ ከአካዝያስ ወንድሞች ጋር ተገናኝቶ። እናንተ እነማን ናችሁ? አለ። እነርሱም። እኛ የአካዝያስ ወንድሞች ነን፤ የንጉሡንና የእቴጌይቱን ልጆች ደኅንነት ለመጠየቅ እንወርዳለን አሉት። |
14. | እርሱም። በሕይወታቸው ያዙአቸው አለ። ያዙአቸውም፥ በበግ ጠባቂዎችም ቤት አጠገብ ባለው ጕድጓድ አርባ ሁለቱን ሰዎች ገደሉአቸው፤ ማንንም አላስቀረም። |
15. | ከዚያም በሄደ ጊዜ የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን ተገናኘው፤ ደኅንነቱንም ጠይቆ። ልቤ ከልብህ ጋር እንደ ሆነ ያህል ልብህ ከልቤ ጋር በቅንነት ነውን? አለው፤ ኢዮናዳብም። እንዲሁ ነው አለው። ኢዩም። እንዲሁ እንደ ሆነስ እጅህን ስጠኝ አለ። እጁንም ሰጠው፤ ወደ ሰረገላውም አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጠውና። |
16. | ከእኔ ጋር ና፥ ለእግዚአብሔርም መቅናቴን እይ አለው። በሰረገላውም አስቀመጠው። |
17. | ወደ ሰማሪያም በመጣ ጊዜ ለኤልያስ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል እስኪያጠፋው ድረስ ከአክዓብ በሰማርያ የቀረውን ሁሉ ገደለ። |
18. | ኢዩም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ። አክዓብ በኣልን በጥቂቱ አመለከው፤ ኢዩ ግን በብዙ ያመልከዋል። |
19. | አሁንም የባኣልን ነቢያት ሁሉ፥ አገልጋዮቹንም ሁሉ፥ ካህናቱንም ሁሉ ወደ እኔ ጥሩ፤ ማንም አይቅር፤ ለባኣል ታላቅ መሥዋዕት አቀርባለሁ፥ የቀረውም ሁሉ በሕይወት አይኖርም አላቸው። ኢዩም የበኣልን አገልጋዮች ያጠፋ ዘንድ በተንኰል ይህን አደረገ። |
20. | ኢዩም። ለበኣል ዋና ጉባኤ ቀድሱ አለ። |
21. | እነርሱም አወጁ። ኢዩም ወደ እስራኤል ሁሉ ላከ፥ የበኣልም አገልጋዮች ሁሉ መጡ፤ ሳይመጣ የቀረ አንድ ስንኳ አልነበረም። ወደ በኣልም ቤት ገቡ፥ የበኣልም ቤት ከዳር እስከ ዳር ድረስ ሞልቶ ነበር፤ |
22. | ዕቃ ቤቱንም። ለበኣል አገልጋዮች ሁሉ ልብስ አውጣ አለው። |
23. | ልብሱንም አወጣላቸው። ኢዩም የሬካብም ልጅ ኢዮናዳብ ወደ በኣል ቤት ገቡ። የበኣልንም አገልጋዮች። መርምሩ፥ ከበኣል አገልጋዮች ብቻ በቀር እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ወገን በእናንተ ዘንድ አንድ እንኳ እንዳይኖር ተመልከቱ አላቸው። |
24. | የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትም ያቀረቡ ዘንድ ገቡ፤ ኢዩም። በእጃችሁ አሳልፌ ከምሰጣችሁ ሰዎች አንድ ሰው ያመለጠ እንደ ሆነ ነፍሱ በዚያ ነፍስ ፋንታ ትሆናለች ብሎ በውጪ ሰማንያ ሰዎችን አዘጋጅቶ ነበር። |
25. | የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አቅርበው በፈጸሙ ጊዜ ኢዩ ዘበኞቹንና አለቆቹን። ግቡና ግደሉአቸው፤ አንድም አይውጣ አላቸው። በሰይፍም ስለት ገደሉአቸው፤ ዘበኞችና አለቆችም ወደ ውጭ ጣሉአቸው፥ ወደ በኣልም ቤት ከተማ ሄዱ። |
26. | ከበኣልም ቤት ሐውልቶቹን አወጡ አቃጠሉአቸውም። |
27. | የበኣልን ሐውልት ቀጠቀጡ፥ የበኣልንም ቤት አፈረሱ፥ እስከ ዛሬም ድረስ የውዳቂ መጣያ አደረጉት። |
28. | እንዲሁም ኢዩ በኣልን ከእስራኤል አጠፋ። |
29. | ነገር ግን እስራኤልን ካሳተው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኃጢአት፥ በቤቴልና በዳን ከነበሩት ከወርቁ እምቦሶች፥ ኢዩ አልራቀም። |
30. | እግዚአብሔርም ኢዩን። በፊቴ ቅን ነገር አድርገሃልና፥ በልቤም ያለውን ሁሉ በአክዓብ ቤት ላይ አድርገሃልና ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣሉ አለው። |
31. | ኢዩ ግን በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ሕግ በፍጹም ልቡ ይሄድ ዘንድ አልተጠነቀቀም፤ እስራኤልንም ካሳተው ከኢዮርብዓም ኃጢአት አልራቀም። |
32. | በዚያም ወራት እግዚአብሔር እስራኤልን ይከፋፍላቸው ዘንድ ጀመረ፤ አዛሄልም በእስራኤል ዳርቻ ሁሉ መታቸው። |
33. | በዮርዳኖስ ምሥራቅ ያለውን የገለዓድን አገር ሁሉ፥ በአርኖን ወንዝ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ የጋድንና የሮቤልን የምናሴንም አገር፥ ገለዓድንና ባሳንን መታ። |
34. | የቀረውም የኢዩ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ ጭከናውም ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? |
35. | ኢዩም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በሰማርያም ቀበሩት። በፋንታውም ልጁ ኢዮአካዝ ነገሠ። |
36. | ኢዩም በሰማርያ በእስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን ሀያ ስምንት ዓመት ነበረ። |
← 2Kings (10/25) → |