← 1Chronicles (22/29) → |
1. | ዳዊትም። ይህ የእግዚአብሔር ቤት ነው፥ ይህም ለእስራኤል ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ ነው አለ። |
2. | ዳዊትም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ይሰበስቡ ዘንድ አዘዘ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ለመሥራት የሚወቀሩትን ድንጋዮች ይወቅሩ ዘንድ ጠራቢዎችን አኖረ። |
3. | ዳዊትም ለበሮቹ ሳንቃ ለሚሆኑ ለምስማርና ለመጠረቂያ ብዙ ብረት፥ ከብዛቱም የተነሣ የማይመዘን ናስ አዘጋጀ። |
4. | ሲዶናውያውንና የጢሮስ ሰዎች ብዙ የዝግባ እንጨት ወደ ዳዊት ያመጡ ነበርና ቍጥር ያሌላቸውን የዝግባ እንጨቶች አዘጋጀ። |
5. | ዳዊትም። ልጄ ሰሎሞን ታናሽና ለጋ ብላቴና ነው፥ ለእግዚአብሔርም የሚሠራው ቤት እጅግ ማለፊያና በአገሩ ሁሉ ስሙና ክብሩ እንዲጠራ ይሆን ዘንድ ይገባል፤ ስለዚህ አዘጋጅለታለሁ አለ። ዳዊትም ሳይሞት አስቀድሞ ብዙ አዘጋጀ። |
6. | ልጁንም ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ አዘዘው። |
7. | ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለ። ልጄ ሆይ፥ እኔ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ቤት እሠራ ዘንድ በልቤ አስቤ ነበር። |
8. | ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ። እጅግ ደም አፍስሰሃል፥ ታላቅም ሰልፍ አድርገሃል፤ በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም። |
9. | እነሆ፥ የዕረፍት ሰው የሚሆን ልጅ ይወለድልሃል፤ በዙሪያው ካሉ ከጠላቶቹ ሁሉ አሳርፈዋለሁ፤ ስሙ ሰሎሞን ይባላልና፥ በዘመኑም ሰላምንና ጸጥታን ለእስራኤል እሰጣለሁ። |
10. | እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፥ ልጅም ይሆነኛል፥ እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ የመንግሥቱንም ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ። |
11. | አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም እንደ ተናገረው ያከናውንልህ፥ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ። |
12. | ብቻ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ሕግ ትጠብቅ ዘንድ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ፥ በእስራኤልም ላይ ያሠልጥንህ። |
13. | እግዚአብሔር ስለ እስራኤል ሙሴን ያዘዘውን ሥርዓትና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ብትጠነቀቅ በዚያን ጊዜ ይከናወንልሃል፤ አይዞህ፥ በርታ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም። |
14. | አሁንም፥ እነሆ፥ በድህነቴ ለእግዚአብሔር ቤት መቶ ሺህ መክሊት ወርቅና አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፥ ሚዛንም የሌላቸው ብዙ ናስና ብረት አዘጋጀሁ፤ ደግሞም እንጨትና ድንጋዮች አዘጋጀሁ፥ አንተም ከዚያ በላይ ጨምር። |
15. | በአንተም ዘንድ ብዙ ሠራተኞች፥ ድንጋይና እንጨት ወቃሪዎችና ጠራቢዎች፥ ሥራውንም ሁሉ ለማድረግ ጠቢባን ሰዎች ሁሉ አሉ። |
16. | የሚሠሩበት ወርቅና ብር ናስና ብረት ቍጥር የለውም፤ ተነሥተህ ሥራ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን። |
17. | ዳዊትም ደግሞ ልጁን ሰሎሞንን ያግዙ ዘንድ የእስራኤልን አለቆች ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው። |
18. | አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይደለምን? በምድርም የሚቀመጡትን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ምድርም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ፊት ተገዝታለችና በዙሪያችሁ ሁሉ ዕረፍትን ሰጥቶአችኋል። |
19. | አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈልጉ ዘንድ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ስጡ፤ ለእግዚአብሔርም ስም ወደሚሠራው ቤት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦትና የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ታመጡ ዘንድ ተነሥታችሁ የአምላክን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ። |
← 1Chronicles (22/29) → |