Zephaniah (2/3)  

2. እናንተ እፍረት የሌላችሁ ሕዝብ ሆይ፥ ትእዛዝ ሳይወጣ፥ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ፥ የእግዚአብሔርም ቍጣ ትኵሳት ሳይመጣባችሁ፥ የእግዚአብሔርም ቍጣ ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ፥ ተከማቹም።
3. እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፥ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቍጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።
4. ጋዛ ትበረበራለች፥ አስቀሎናም ባድማ ትሆናለች፤ አዞጦንንም በቀትር ወደ ውጭ ያሳድዱአታል፥ አቃሮንም ትነቀላለች።
5. በባሕር ዳር ለሚኖሩ ለከሊታውያን ሕዝብ ወዮላቸው! የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፥ የእግዚአብሔር ቃል በአንተ ላይ ነው፥ የሚቀመጥብህም ሰው እንዳይኖር አጠፋሃለሁ።
6. ቀርጤስም የእረኞች መኖሪያና የመንጎች በረት ይሆናል።
7. የባሕሩም ዳር ለይሁዳ ቤት ቅሬታ ይሆናል፥ በዚያም ይሰማራሉ፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ይጐበኛቸዋልና፥ ምርኮአቸውንም ይመልሳልና በአስቀሎና ቤቶች ውስጥ ማታ ይተኛሉ።
8. በሕዝቤም ላይ ያላገጡባትን፥ በድንበራቸውም ላይ እየታበዩ የተናገሩባትን የሞዓብን ማላገጥና የአሞንን ልጆች ስድብ ሰምቻለሁ።
9. ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና በእርግጥ ሞዓብ እንደ ሰዶም፥ የአሞንም ልጆች እንደ ገሞራ፥ የሳማ ስፍራና የጨው ጕድጓድ ለዘላለምም ምድረ በዳ ሆነው ይኖራሉ፤ የሕዝቤም ቅሬታ ይበዘብዛቸዋል፥ ከወገኔም የተረፉት ይወርሱአቸዋል።
10. በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ አላግጠዋልና፥ እየታበዩም ተናግረዋልና ይህ ስለ ትዕቢታቸው ያገኛቸዋል።
11. እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የተፈራ ይሆናል፥ የምድርንም አማልክት ሁሉ ያከሳቸዋል፤ በአሕዛብም ደሴቶች ሁሉ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በስፍራቸው ሆነው ለእርሱ ይሰግዳሉ።
12. እናንተም ኢትዮጵያውያን ደግሞ፥ በሰይፌ ትገደላላችሁ።
13. እርሱም በሰሜን ላይ እጁን ይዘረጋል፥ አሦርንም ያጠፋል፤ ነነዌንም ባድማ፥ እንደ በረሃም ደረቅ ያደርጋታል።
14. መንጎችም የምድርም አራዊት ሁሉ በውስጥዋ ይመሰጋሉ፤ ይብራና ጃርት በዓምዶችዋ መካከል ያድራሉ፤ ድምፃቸው በመስኮቶችዋ ይጮኻል፤ የዝግባም እንጨት ሥራ ይገለጣልና በመድረኮችዋ ላይ ጥፋት ይሆናል።
15. ተዘልላ የተቀመጠች፥ በልብዋም። እኔ ነኝ፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለም ያለች ደስተኛይቱ ከተማ ይህች ናት፤ አራዊት የሚመሰጉባት ባድማ እንዴት ሆነች! በእርስዋ በኩል የሚያልፈው ሁሉ እጁን እያወዛወዘ ያፍዋጫል።

  Zephaniah (2/3)