← Zechariah (9/14) → |
1. | የእግዚአብሔር ቃል ሸክም በሴድራክ ምድር ላይ ነው፥ በደማስቆም ላይ ያርፋል፤ የእግዚአብሔር ዓይን ወደ ሰውና ወደ እስራኤል ነገድ ሁሉ ዘንድ ነው፤ |
2. | ደግሞም በዳርቻዋ ባለችው በሐማት ላይ፥ እጅግ ጠቢበኞች በሆኑ በጢሮስና በሲዶና ላይ ነው። |
3. | ጢሮስም ምሽግን ለራስዋ ሠርታለች፥ ብሩንም እንደ አፈር ጥሩውንም ወርቅ እንደ መንገድ ጭቃ አከማችታለች። |
4. | እነሆ፥ ጌታ ይገፍፋታል፥ በባሕርም ላይ ያለውን ብርታትዋን ይመታል፤ እርስዋም በእሳት ትበላለች። |
5. | አስቀሎና አይታ ትፈራለች፤ ጋዛ ደግሞ አይታ እጅግ ትታመማለች፤ አቃሮንም እንዲሁ፥ ተስፋዋ ይቈረጣልና፤ ንጉሡም ከጋዛ ይጠፋል፥ በአስቀሎናም የሚቀመጥ አይገኝም። |
6. | የተደባለቀ ወገን በአዛጦን ይቀመጣል፥ የፍልስጥኤማውያንንም ትዕቢት አጠፋለሁ። |
7. | ደሙንም ከአፉ ውስጥ ርኩሱንም ነገር ከጥርሱ መካከል አስወግዳለሁ፤ እርሱም ደግሞ ለአምላካችን ቅሬታ ይሆናል፤ በይሁዳም እንደ አለቃ ይሆናል፥ አቃሮንም እንደ ኢያቡሳዊ ይሆናል። |
8. | እኔም ማንም እንዳይሄድና እንዳይመለስ እንደ ጠባቂ ጦር ሆኖ በቤቴ ዙሪያ ሰፈር አደርጋለሁ፤ አሁንም በዓይኔ አይቻለሁና ከዚህ በኋላ አስጨናቂ አያልፍባቸውም። |
9. | አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል። |
10. | ሰረገላውንም ከኤፍሬም ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም አጠፋለሁ፤ የሰልፉም ቀስት ይሰበራል፥ ለአሕዛብም ሰላምን ይናገራል፤ ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፥ ከወንዙም እስከ ምድር ዳርቻ ድርስ ይሆናል። |
11. | ለአንቺም ደግሞ ስለ ቃል ኪዳንሽ ደም፥ እስሮችሽን ውኃ ከሌለበት ጕድጓድ አውጥቻለሁ። |
12. | እናንተ በተስፋ የምትኖሩ እስሮች ሆይ፥ ወደ ጽኑ አምባ ተመለሱ፤ ሁለት እጥፍ አድርጌ እንድመልስልሽ ዛሬ እነግርሻለሁ። |
13. | ይሁዳን ለእኔ ገትሬአለሁ፤ ቀስቱን በኤፍሬም ሞልቼአለሁ፤ ጽዮን ሆይ፥ ልጆችሽን በግሪክ ልጆች ላይ አስነሣለሁ፥ አንቺንም እንደ ኃያል ሰው ሰይፍ አደርግሻለሁ። |
14. | እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ይገለጣል፥ ፍላጻውም እንደ መብረቅ ይወጣል፤ ጌታ እግዚአብሔርም መለከትን ይነፋል፥ በደቡብም ዐውሎ ነፋስ ይሄዳል። |
15. | የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይጠብቃቸዋል፤ እነርሱም ይበሉአቸዋል፥ የወንጭፉንም ድንጋዮች ይረግጣሉ፤ እንደ ወይን ጠጅም ይጠጡአቸዋል፥ እንደ ጥዋዎችም እንደ መሠዊያም ማዕዘኖች የተሞሉ ይሆናሉ። |
16. | በዚያም ቀን አምላካቸው እግዚአብሔር እንደ ሕዝቡ መንጋ ያድናቸዋል፤ እነርሱም ለአክሊል እንደሚሆኑ እንደ ከበሩ ድንጋዮች ይሆናሉ፥ በምድሩም ላይ ይብለጨለጫሉ። |
17. | በጎነቱ እንዴት ታላቅ ነው! ውበቱስ እንዴት ታላቅ ነው! እህል ጐበዛዝቱን፥ ጉሽ ጠጅም ቈነጃጅቱን ያለመልማል። |
← Zechariah (9/14) → |