Zechariah (8/14)  

1. የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2. የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ ጽዮን ታላቅ ቅንዓት ቀንቻለሁ፥ በታላቅም ቍጣ ስለ እርስዋ ቀንቻለሁ።
3. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ጽዮን ተመልሻለሁ፥ በኢየሩሳሌምም መካከል እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፤ የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ተራራ የተቀደሰ ተራራ ይባላል።
4. የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዳግመኛ ሽማግሌዎችና ባልቴቶች በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቀመጣሉ፤ ሰውም ሁሉ ከዕድሜው ብዛት የተነሣ ምርኩዝ በእጁ ይይዛል።
5. የከተማይቱም አደባባዮች በእነዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ።
6. የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህ ወራት በዚህ ሕዝብ ቅሬታ ዓይን ዘንድ ድንቅ ቢሆን፥ በውኑ በእኔ ዓይን ዘንድ ደግሞ ድንቅ ይሆናልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
7. የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሕዝቤን ከምሥራቅ ምድርና ከምዕራብ ምድር አድነዋለሁ፤
8. አመጣቸዋለሁም፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ይኖራሉ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፥ እኔም በእውነትና በጽድቅ አምላክ እሆናቸዋለሁ።
9. የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። መቅደሱ ይሠራ ዘንድ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቤት ከተመሠረተበት ቀን ጀምሮ ከነቢያት አፍ ይህን ቃል በዚህ ዘመን የሰማችሁ እናንተ ሆይ፥ እጃችሁን አበርቱ።
10. ከዚያ ወራት አስቀድሞ ለሰውና ለእንስሳ ዋጋ አልነበረምና፤ እኔም ሰውን ሁሉ በወንድሙ ላይ አስነሥቼ ነበርና ከአስጨናቂው የተነሣ ለሚገባውና ለሚወጣው ሰላም አልነበረም።
11. አሁን ግን እንደ ቀደመው ዘመን በዚህ ሕዝብ ቅሬታ ላይ አልሆንም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
12. ነገር ግን ሰላምን እዘራለሁ፤ ወይኑ ፍሬውን ይሰጣል፥ ምድርም አዝመራዋን ታወጣለች፥ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፤ ለዚህም ሕዝብ ቅሬታ ይህን ነገር ሁሉ አወርሳለሁ።
13. የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ አድናችኋለሁ፥ በረከትም ትሆናላችሁ፤ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ።
14. የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። አባቶቻችሁ እጅግ ባስቈጡኝ ጊዜ ክፉ ለማድረግ እንዳሰብሁ፥ እንዳልተጸጸትሁም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥
15. እንዲሁ ዳግመኛ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ቤት በዚህ ወራት በጎነትን አደርግ ዘንድ አስቤአለሁ፤ አትፍሩ።
16. የምትሠሩት ነገር ይህ ነው፤ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ በበር አደባባያችሁም የእውነትንና የሰላምን ፍርድ ፍረዱ፤
17. ሁላችሁም በባልንጀራችሁ ላይ ክፉን ነገር በልባችሁ አታስቡ፤ የሐሰትንም መሐላ አትውደዱ፤ ይህን ነገር ሁሉ እጠላለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
18. የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
19. የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሤትም በዓላት ይሆናል፤ ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ።
20. የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በብዙ ከተሞች የሚቀመጡ አሕዛብ ገና ይመጣሉ፤
21. በአንዲትም ከተማ የሚኖሩ ሰዎች። እግዚአብሔርን እንለምን ዘንድ፥ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን እንፈልግ ዘንድ ኑ እንሂድ፤ እኔም እሄዳለሁ እያሉ ወደ ሌላ ከተማ ይሄዳሉ።
22. ብዙ ወገኖችና ኃይለኞች አሕዛብ በኢየሩሳሌም የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ፥ እግዚአብሔርንም ይለምኑ ዘንድ ይመጣሉ።
23. የሠራዊትም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚያ ዘመን ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ አሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ ይላሉ።

  Zechariah (8/14)