| ← Zechariah (6/14) → |
| 1. | ተመልሼም ዓይኖቼን አነሣሁ፥ እነሆም፥ አራት ሰረገሎች ከሁለት ተራራ መካከል ሲወጡ አየሁ፤ ተራሮቹም የናስ ተራሮች ነበሩ። |
| 2. | በፊተኛው ሰረገላ መጋላ ፈረሶች፥ በሁለተኛውም ሰረገላ ዱሪ ፈረሶች ነበሩ፥ |
| 3. | በሦስተኛውም ሰረገላ አምባላይ ፈረሶች፥ በአራተኛውም ሰረገላ ቅጥልጣል ፈረሶች ነበሩ። |
| 4. | ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ። ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት። |
| 5. | መልአኩም መልሶ። እነዚህ በምድር ሁሉ ጌታ ፊት ከቆሙበት ስፍራ የሚወጡ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ናቸው። |
| 6. | ዱሪ ፈረሶች ያሉበት ወደ ሰሜን ይወጣል፤ አምባላዮቹም ከእነርሱ በኋላ ይወጣሉ፥ ቅጥልጣሎችም ወደ ደቡብ ይወጣሉ አለኝ። |
| 7. | መጋላዎቹም ደግሞ ወጡ በምድርም ይመላለሱ ዘንድ ለመሄድ ይፈልጉ ነበር፤ እርሱም። ሂዱ፥ በምድር ላይ ተመላለሱ አለ። እነርሱም በምድር ላይ ተመላለሱ። |
| 8. | ጮኾም። እነሆ፥ ወደ ሰሜን ምድር የሚወጡት እነርሱ መንፈሴን በሰሜን ምድር ላይ አሳርፈዋል ብሎ ተናገረኝ። |
| 9. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
| 10. | ከባቢሎን ከመጡት ምርኮኞች ከሔልዳይና ከጦብያ ከዮዳኤም ውሰድ፤ በዚያም ቀን መጥተህ ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ግባ። |
| 11. | ብርንና ወርቅን ከእነርሱ ውሰድ፥ አክሊሎችንም ሥራ፤ በታላቁም ካህን በኢዮሴዴቅ ልጅ በኢያሱ ራስ ላይ ድፋቸው፥ |
| 12. | እንዲህም በለው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ስሙ ቍጥቋጥ የሚባል ሰው በስፍራው ይበቅላል፥ የእግዚአብሔርንም መቅደስ ይሠራል። |
| 13. | እርሱ የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሠራል፥ ክብርንም ይሸከማል፥ በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይነግሣል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፥ የሰላምም ምክር በሁለቱ መካከል ይሆናል። |
| 14. | አክሊሎችም ለሔሌምና ለጦብያ ለዮዳኤም ለሶፎንያስም ልጅ ለሔን በእግዚአብሔር መቅደስ ውስጥ ለመታሰቢያ ይሆናሉ። |
| 15. | በሩቅም ያሉት መጥተው የእግዚአብሔርን መቅደስ ይሠራሉ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቃችሁ ብትሰሙ ይህ ይሆናል። |
| ← Zechariah (6/14) → |