| ← Zechariah (4/14) → |
| 1. | ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ተመልሶ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው አነቃኝ። |
| 2. | እርሱም። የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። እነሆ፥ ሁለንተናው ወርቅ የሆነውን መቅረዝ አየሁ፤ የዘይትም ማሰሮ በራሱ ላይ ነበረ፥ ሰባትም መብራቶች ነበሩበት፤ በራሱም ላይ ለነበሩት መብራቶች ሰባት ቧንቧዎች ነበሩአቸው። |
| 3. | ሁለት የወይራ ዛፎች፥ አንዱ በማሰሮው በስተ ቀኝ አንዱም በስተ ግራው ሆነው፥ በአጠገቡ ነበሩ አልሁ። |
| 4. | ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ። ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድር ናቸው? አልሁት። |
| 5. | ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውም መልአክ መልሶ። እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን? አለኝ። እኔም። ጌታዬ ሆይ፥ አላውቅም አልሁ። |
| 6. | መልሶም። ለዘሩባቤል የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። |
| 7. | ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ምንድር ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፤ ሰዎችም። ሞገስ፥ ሞገስ ይሁንለት ብለው እየጮኹ እርሱ መደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል ብሎ ተናገረኝ። |
| 8. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። |
| 9. | የዘሩባቤል እጆች ይህን ቤት መሠረቱ፥ የእርሱም እጆች ይፈጽሙታል፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። |
| 10. | የጥቂቱን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው? እነዚህ ሰባቱ ደስ ብሎአቸው በዘሩባቤል እጅ ቱንቢውን ያያሉ፤ እነዚህም በምድር ሁሉ የሚዘዋወሩ የእግዚአብሔር ዓይኖች ናቸው። |
| 11. | እኔም መልሼ። በመቅረዙ በስተ ቀኝና በስተ ግራ ያሉ እነዚህ ሁለት የወይራ ዛፎች ምንድር ናቸው? አልሁት። |
| 12. | ሁለተኛም መልሼ። በሁለቱ የወርቅ ቧንቧዎች አጠገብ ሆነው የወርቁን ዘይት የሚያፈስሱ እነዚህ ሁለት የወይራ ቅርንጫፎች ምንድር ናቸው? አልሁት። |
| 13. | እርሱም መልሶ። እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን? አለኝ። እኔም ። ጌታዬ ሆይ፥ አላውቅም አልሁት። |
| 14. | እርሱም። በምድር ሁሉ ጌታ አጠገብ የቆሙት ሁለቱ የተቀቡት እነዚህ ናቸው አለኝ። |
| ← Zechariah (4/14) → |