Zechariah (12/14)  

1. ስለ እስራኤል የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ሸክም ይህ ነው። ሰማያትን የዘረጋ፥ ምድርንም የመሠረተ፥ የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
2. እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ላሉት ለአሕዛብ ሁሉ የመንገድገድ ዋንጫ አደርጋታለሁ፤ ደግሞም ኢየሩሳሌም ስትከበብ በይሁዳ ላይ እንዲሁ ይሆናል።
3. በዚያም ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፤ የሚሸከሙአት ሁሉ እጅግ ይቈስላሉ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በላይዋ ላይ ይከማቻሉ።
4. በዚያ ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ፈረስን ሁሉ በድንጋጤ፥ ተቀማጭንም በእብድነት እመታለሁ፤ ዓይኖቼንም በይሁዳ ላይ እከፍታለሁ፥ የአሕዛብንም ፈረሶች ሁሉ በዕውርነት እመታለሁ።
5. የይሁዳም አለቆች በልባቸው። በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ በአምላካቸው በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ብርታት አለ ይላሉ።
6. በዚያ ቀን የይሁዳን አለቆች በእንጨት መካከል እንዳለ ትንታግ፥ በነዶችም መካከል እንዳለ እንደ ፋና ነበልባል አደርጋቸዋለሁ፤ በቀኝና በግራ በዙሪያ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይበላሉ፤ ከዚያም ወዲያ ኢየሩሳሌም በስፍራዋ በኢየሩሳሌም ትኖራለች።
7. እግዚአብሔርም የዳዊት ቤት ክብርና የኢየሩሳሌም ሰዎች ክብር በይሁዳ ክብር ላይ እንዳይታበይ የይሁዳን ድንኳኖች አስቀድሞ ያድናል።
8. በዚያ ቀን እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ይመክትላቸዋል፤ በዚያም ቀን ከእነርሱ መካከል ደካማው እንደ ዳዊት ይሆናል፤ የዳዊትም ቤት በፊታቸው እንደ እግዚአብሔር መልአክ እንደ አምላክ ይሆናል።
9. በዚያም ቀን በኢየሩሳሌም ላይ የሚመጡትን አሕዛብ ሁሉ ለማጥፋት እጋደላለሁ።
10. በዳዊትም ቤት ላይ፥ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ላይ፥ የሞገስንና የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ፤ ወደ እርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ፤ ሰውም ለአንድያ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኀዘን ያዝኑለታል።
11. በዚያ ቀን በመጊዶን ሜዳ እንደ ነበረው እንደ ሐዳድሪሞን ልቅሶ ታላቅ ልቅሶ በኢየሩሳሌም ይሆናል።
12. ምድሪቱም ታለቅሳለች፤ እያንዳንዱ ወገን ለብቻው፥ የዳዊት ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤ የናታን ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤
13. የሌዊ ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤ የሰሜኢ ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤
14. የቀሩት ወገኖች ሁሉ እያንዳንዱ ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው ያለቅሳሉ።

  Zechariah (12/14)