← Zechariah (11/14) → |
1. | ሊባኖስ ሆይ፥ ደጆችህን ክፈት፥ እሳትም ዝግባዎችህን ትብላ። |
2. | የጥድ ዛፍ ሆይ፥ ዝግባ ወድቆአልና፥ ከበርቴዎችም ጠፍተዋልና ዋይ በል፤ እናንተም የባሳን ዛፎች ሆይ፥ ጽኑው ጫካ ተቈርጦአልና ዋይ በሉ። |
3. | የእረኞች ክብር ተዋርዶአልና የዋይታቸው ድምፅ ተሰምቶአል፤ የዮርዳኖስ ትዕቢት ተዋርዶአልና የአንበሶች ግሣት ድምፅ ተሰምቶአል። |
4. | አምላኬ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል። ለእርድ የሚሆኑትን በጎች ጠብቅ። |
5. | የገዙአቸው ያርዱአቸዋል፥ ራሳቸውንም እንደ በደለኞች አድርገው አይቈጥሩም፤ የሸጡአቸውም። ባለ ጠጋ ሆነናልና እግዚአብሔር ይመስገን ይላሉ፤ እረኞቻቸውም አይራሩላቸውም። |
6. | ከእንግዲህ ወዲህ በምድር ላይ ለሚኖሩ አልራራም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እነሆም፥ ሰውን ሁሉ በባልንጀራውና በንጉሡ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ምድሪቱንም ይመታሉ፥ ከእጃቸውም አላድናቸውም። |
7. | እኔም ለእርድ የሚሆኑትን በጎች፥ የመንጋውን ችግረኞች ጠበቅሁ። ሁለት በትሮችንም ወሰድሁ፤ የአንዲቱን ስም ውበት የሁለተኛይቱንም ስም ማሰሪያ ብዬ ጠራሁ፤ መንጋውንም ጠበቅሁ። |
8. | በአንድ ወርም ሦስቱን እረኞች አጠፋሁ፤ ነፍሴም ተሰቀቀቻቸው፥ ነፍሳቸውም ደግሞ እኔን ጠላች። |
9. | እኔም። እናንተን አልጠብቅም፤ የሚሞተው ይሙት፥ የሚጠፋውም ይጥፋ፤ የቀረውም እያንዳንዱ የባልንጀራውን ሥጋ ይብላ አልሁ። |
10. | እኔም ከሕዝቦች ሁሉ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አፈርስ ዘንድ ውበት የተባለችውን በትሬን ወስጄ ቈረጥሁ። |
11. | በዚያም ቀን ተሰበረች፤ እንዲሁም እኔን የተመለከቱ የመንጋው ችግረኞች የእግዚአብሔር ቃል እንደ ነበረ አወቁ። |
12. | እኔም። ደስ ብሎአችሁ እንደ ሆነ ዋጋዬን ስጡኝ፤ ያለዚያ ግን ተዉት አልሁ። እነርሱም ለዋጋዬ ሠላሳ ብር መዘኑ። |
13. | እግዚአብሔርም። የተስማሙበትን የከበረውን ዋጋዬን በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኑረው አለኝ። እኔም ሠላሳውን ብር ወስጄ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኖርሁት። |
14. | በይሁዳና በእስራኤል መካከል ያለውንም ወንድማማችነት እሰብር ዘንድ ማሰሪያ የተባለችውን ሁለተኛይቱን በትሬን ቈረጥሁ። |
15. | እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ዳግመኛም የሰነፍን እረኛ ዕቃ ውሰድ። |
16. | እነሆ፥ በአገሩ ውስጥ እረኛ አስነሣለሁ፤ እርሱም የጠፋውን አያስብም፥ የባዘነውን አይፈልግም፥ የተሰበረውን አይጠግንም፤ የዳነውንም አይቀልብም፥ ነገር ግን የሰባውን ሥጋ ይበላል፥ ሰኰናውንም ይቀለጣጥማል። |
17. | መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት! ሰይፍ በክንዱና በቀኝ ዓይኑ ላይ ይሆናል፤ ክንዱም አጥብቃ ትደርቃለች፥ ቀኝ ዓይኑም ፈጽሞ ትጨልማለች። |
← Zechariah (11/14) → |