Zechariah (10/14)  

1. በኋለኛው ዝናብ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዝናቡን ለምኑ፤ እግዚአብሔር መብረቅ ያደርጋል፤ እርሱም የበልግ ዝናብን ለእያንዳንዱም በሜዳ ውስጥ ሣርን ይሰጣል።
2. ተራፊም ከንቱነትን ተናግረዋልና፥ ምዋርተኞችም ውሸትን አይተዋልና፤ ሕልምንም የሚያዩ በሐሰት ተናግረዋል፥ በከንቱም ያጽናናሉ፤ እረኛም የላቸውምና እንደ በጎች ተቅበዝብዘዋል ተጨንቀውማል።
3. ቍጣዬ በእረኞች ላይ ነድዶአል፥ አውራ ፍየሎችንም እቀጣለሁ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም የይሁዳን ቤት መንጋውን ጐብኝቶአል፥ በሰልፍም ውስጥ እንዳለ እንደ ክብሩ ፈረስ ያደርጋቸዋል።
4. ከእርሱ ዘንድ የማዕዘኑ ድንጋይ፥ ከእርሱም ዘንድ ችንካሩ፥ ከእርሱም ዘንድ የሰልፉ ቀስት፥ ከእርሱም ዘንድ አስገባሪው ሁሉ በአንድ ላይ ይመጣሉ።
5. በሰልፍም ጊዜ ጠላቶቻቸውን በመንገድ ጭቃ ውስጥ እንደሚረግጡ ኃያላን ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነውና ይዋጋሉ፥ ፈረሰኞችም ያፍራሉ።
6. ወድጃቸዋለሁና የይሁዳን ቤት አበረታለሁ፥ የዮሴፍንም ቤት አድናለሁ፤ አደላድላቸዋለሁም፤ እመልሳቸዋለሁ፤ እኔም አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝና፥ እኔም እሰማቸዋለሁና እንዳልጣልኋቸው ይሆናሉ።
7. የኤፍሬምም ሰዎች እንደ ኃያላን ይሆናሉ፥ ልባቸውም የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰው ደስ ይለዋል፤ ልጆቻቸውም አይተው ደስ ይላቸዋል፥ ልባቸውም በእግዚአብሔር ሐሤት ያደርጋል።
8. ተቤዥቼአቸዋለሁና በፉጨት ጠርቼ እሰበስባቸዋለሁ፤ ቀድሞም በዝተው እንደ ነበሩ ይበዛሉ።
9. በአሕዛብም መካከል ብዘራቸው እንኳ በሩቅ አገር ሳሉ ያስቡኛል፥ ከልጆቻቸውም ጋር በሕይወት ይኖራሉ፥ ይመለሱማል።
10. ከግብጽም ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ ከአሦርም እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገለዓድና ወደ ሊባኖስ ምድር አመጣቸዋለሁ፥ የሚበቃም ቦታ አይገኝላቸውም።
11. እርሱም በጭንቅ ባሕር ያልፋል፥ የባሕርንም ሞገድ ይመታል፥ የወንዙም ጥልቅ ሁሉ ይደርቃል፤ የአሦርም ትዕቢት ይዋረዳል፥ የግብጽም በትረ መንግሥት ይርቃል።
12. በአምላካቸው በእግዚአብሔር አበረታቸዋለሁ፥ በስሙም ይመካሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።

  Zechariah (10/14)