SongOfSongs (3/8)  

1. ሌሊት በምንጣፌ ላይ ነፍሴ የወደደችውን ፈለግሁት፤ ፈለግሁት አላገኘሁትም።
2. እነሣለሁ በከተማይቱም እዞራለሁ፥ ነፍሴ የወደደችውን በጎዳናና በአደባባይ እፈልጋለሁ፤ ፈለግሁት አላገኘሁትም።
3. ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፤ ነፍሴ የወደደችውን አያችሁትን? አልኋቸውም።
4. ከእነርሱም ጥቂት እልፍ ብዬ ነፍሴ የወደደችውን አገኘሁት፥ ያዝሁትም ወደ እናቴም ቤት ወደ ወላጅ እናቴም እልፍኝ እስካገባው ድረስ አልተውሁትም።
5. እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሡትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አምላችኋለሁ።
6. መዓዛም እንደ ከርቤና እንደ ዕጣን የሆነችው፥ ከልዩ ከነጋዴ ቅመም ሁሉ የሆነችው፥ ይህች ከምድረ በዳ እንደ ጢስ ምስሶ የወጣችው ማን ናት?
7. እነሆ፥ የሰሎሞን አልጋ ናት፤ ከእስራኤል ኃያላን ስድሳ ኃያላን በዙሪያው ናቸው።
8. ሁሉም ሰይፍ የያዙ ሰልፈኞች ናቸው፤ በሌሊት ከሚወድቀው ፍርሃት የተነሣ ሰው ሁሉ ሰይፉ በወገቡ አለ።
9. ንጉሡ ሰሎሞን መሸከሚያን ከሊባኖስ እንጨት ለራሱ አሠራ።
10. ምሰሶቹን የብር፥ መደገፊያውንም የወርቅ፥ መቀመጫውንም ሐምራዊ ግምጃ አደረገ፤ ውስጡ በኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ፍቅር የተለበጠ ነው።
11. እናንተ የጽዮን ቈነጃጅት፥ ውጡ፤ እናቱ በሠርጉ ቀንና በልቡ ደስታ ቀን ያደረገችለትን አክሊል ደፍቶ ንጉሥ ሰሎሞንን እዩ።

  SongOfSongs (3/8)