| ← Revelation (8/22) → |
| 1. | ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ እኵል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ። |
| 2. | በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፥ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው። |
| 3. | ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። |
| 4. | የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ። |
| 5. | መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ። |
| 6. | ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ። |
| 7. | ፊተኛውም መልአክ ነፋ፤ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፥ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ። |
| 8. | ሁለተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ፤ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ |
| 9. | በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ። |
| 10. | ሦስተኛውም መልአክ ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፥ በወንዞችና በውኃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ። የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል። |
| 11. | የውኃውም ሲሶ መራራ ሆነ መራራም ስለተደረገ በውኃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ። |
| 12. | አራተኛውም መልአክ ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፥ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት። |
| 13. | አየሁም፥ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ። ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፥ ወዮላቸው፥ ወዮላቸው ሲል ሰማሁ። |
| ← Revelation (8/22) → |