| ← Revelation (7/22) → |
| 1. | ከዚህም በኋላ በአራቱ በምድር ማዕዘን ቆመው አራት መላእክት አየሁ፥ እነርሱም ነፋስ በምድር ቢሆን ወይም በባሕር ወይም በማንም ዛፍ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ። |
| 2. | የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፥ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ። |
| 3. | የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጕዱ አላቸው። |
| 4. | የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። |
| 5. | ከይሁዳ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፥ ከሮቤል ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ |
| 6. | ከአሴር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ |
| 7. | ከምናሴ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከስምዖን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ |
| 8. | ከዛብሎን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ። |
| 9. | ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ |
| 10. | በታላቅም ድምፅ እየጮሁ። በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ። |
| 11. | መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፥ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ። |
| 12. | አሜን፥ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን አሉ። |
| 13. | ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ። እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ። |
| 14. | እኔም። ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁት። አለኝም። እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። |
| 15. | ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፥ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፥ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል። |
| 16. | ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፥ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፤ |
| 17. | በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል። |
| ← Revelation (7/22) → |