| ← Revelation (13/22) → |
| 1. | አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፥ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ። |
| 2. | ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፥ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው። |
| 3. | ከራሶቹም ለሞት እንደ ታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፥ ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፥ |
| 4. | ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም። አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት። |
| 5. | ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። |
| 6. | እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። |
| 7. | ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። |
| 8. | ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል። |
| 9. | ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። |
| 10. | ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል። የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው። |
| 11. | ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር። |
| 12. | በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል። ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰለት ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል። |
| 13. | እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰው ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል። |
| 14. | በአውሬውም ፊት ያደርግ ዘንድ ከተሰጡት ምልክቶች የተነሣ በምድር የሚኖሩትን ያስታል፤ የሰይፍም ቍስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል። |
| 15. | የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው። |
| 16. | ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥ |
| 17. | የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። |
| 18. | አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው። |
| ← Revelation (13/22) → |