| ← Revelation (12/22) → |
| 1. | ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። |
| 2. | እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች። |
| 3. | ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፥ |
| 4. | ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ። |
| 5. | አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። |
| 6. | ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች። |
| 7. | በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ |
| 8. | ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። |
| 9. | ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። |
| 10. | ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል። አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና። |
| 11. | እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፥ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም። |
| 12. | ስለዚህ፥ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፥ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና። |
| 13. | ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት። |
| 14. | ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሀ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት። |
| 15. | እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ። |
| 16. | ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው። |
| 17. | ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤ |
| ← Revelation (12/22) → |