Obadiah (1/1)    

1. የአብድዩ ራእይ። ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶምያስ እንዲህ ይላል። ከእግዚአብሔር ዘንድ ወሬ ሰምተናል፤ መልእክተኛ ወደ አሕዛብ ተልኮ። ተነሡ፥ በላይዋም በሰልፍ እንነሣ ብሎአል።
2. እነሆ፥ በአሕዛብ ዘንድ ታናሽ አድርጌሃለሁ፤ አንተ እጅግ ተንቀሃል።
3. በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር፥ ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ፥ በልብህም። ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው? የምትል አንተ ሆይ፥ የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል።
4. እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፥ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
5. ሌቦች ቢመጡብህ ወይም ወንበዴዎች በሌሊት ቢመጡ፥ የሚበቃቸውን የሚሰርቁ አይደሉምን? ወይንንም የሚቈርጡ ወደ አንተ ቢመጡ ቃርሚያ አያስቀሩምን?
6. አንተ ግን ምንኛ ጠፋህ! ዔሳው ምንኛ ተመረመረ! የተሸሸገበት ነገር ምንኛ ተፈለገ!
7. የተማማልሃቸው ሰዎች ሁሉ ወደ ዳርቻህ ሰደዱህ፤ የታመንሃቸው ሰዎች አታለሉህ፥ አሸነፉህም፤ በበታችህም አሽክላ ዘረጉብህ፥ እነርሱም ማስተዋል የላቸውም።
8. በዚያ ቀን ከኤዶምያስ ጥበበኞችን፥ ከዔሳውም ተራራ ማስተዋልን አላጠፋምን? ይላል እግዚአብሔር።
9. ቴማን ሆይ፥ ሰዎች ሁሉ ከዔሳው ተራራ በመገደል ይጠፉ ዘንድ ኃያላንህ ይደነግጣሉ።
10. በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለ ተደረገ ግፍ እፍረት ይከድንሃል፥ ለዘላለምም ትጠፋለህ።
11. በፊቱ አንጻር በቆምህ ቀን፥ አሕዛብ ጭፍራውን በማረኩበት፥ እንግዶችም በበሩ በገቡበት፥ በኢየሩሳሌምም ዕጣ በተጣጣሉበት ቀን አንተ ደግሞ ከእነርሱ እንደ አንዱ ነበርህ።
12. ነገር ግን በመከራው ቀን ወንድምህን ትመለከት ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን በይሁዳ ልጆች ላይ ደስ ይልህ ዘንድ፥ በጭንቀትም ቀን በትዕቢት ትናገር ዘንድ አይገባህም ነበር።
13. በጥፋታቸውም ቀን በሕዝቤ በር ትገባ ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን መከራቸውን ትመለከት ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን በሀብታቸው ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ አይገባህም ነበር።
14. የሸሹትንም ለመግደል በመንታ መንገድ ላይ ትቆም ዘንድ፥ በጭንቀትም ቀን ከእርሱ የቀሩትን አሳልፈህ ትሰጥ ዘንድ አይገባህም ነበር።
15. የእግዚአብሔር ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቦአልና፤ አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል።
16. በቅዱስ ተራራዬ ላይ እንደ ጠጣችሁ እንዲሁ አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ፤ አዎን ይጠጣሉ፥ ይጨልጡማል፥ እንዳልሆኑም ይሆናሉ።
17. ነገር ግን በጽዮን ተራራ ላይ የሚያመልጡ ይሆናሉ፥ እርሱም ቅዱስ ይሆናል፤ የያዕቆብም ቤት ሰዎች ርስታቸውን ይወርሳሉ።
18. እግዚአብሔርም ተናግሮአልና የያዕቆብ ቤት እሳት፥ የዮሴፍ ቤት ነበልባልም፥ የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናሉ፤ እነርሱንም ያቃጥሉአቸዋል ይበሉአቸውማል፤ ከዔሳውም ቤት ቅሬታ የለውም።
19. የደቡብም ሰዎች የዔሳውን ተራራ፥ የቈላውም ሰዎች ፍልስጥዔማውያንን ይወርሳሉ፤ የኤፍሬምንም አገር የሰማርያንም አገር ይወርሳሉ፤ ብንያምም ገለዓድን ይወርሳል።
20. ይህም የእስራኤል ልጆች የጭፍራቸው ምርኮ የከነዓንን ስፍራ ሁሉ እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳል፤ በስፋራድም የሚኖሩ የኢየሩሳሌም ምርኮኞች የደቡብን ከተሞች ይወርሳሉ።
21. በዔሳውም ተራራ ላይ ይፈርዱ ዘንድ አዳኞች ወደ ጽዮን ተራራ ላይ ይወጣሉ፤ መንግሥቱም ለእግዚአብሔር ይሆናል።

      Obadiah (1/1)