← Numbers (8/36) → |
1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
2. | መብራቶቹን ስትለኵስ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ያበራሉ ብለህ ለአሮን ንገረው። |
3. | አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ በመቅረዙ ፊት መብራቶቹን ለኰሰ። |
4. | መቅረዙም እንዲህ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ተሠራ፤ እስከ አገዳውና እስከ አበቦቹ ድረስ ከተቀጠቀጠ ሥራ ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳሳየው ምሳሌ መቅረዙን እንዲሁ አደረገ። |
5. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
6. | ከእስራኤል ልጆች መካከል ሌዋውያንን ወስደህ አንጻቸው። |
7. | ታነጻቸው ዘንድ እንዲህ ታደርግላቸዋለህ፤ ኃጢአትን የሚያነጻውን ውኃ እርጫቸው፥ በገላቸውም ሁሉ ምላጭ ያሳልፉ፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፥ ይታጠቡም። |
8. | ወይፈንን፥ ለእህሉም ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄትን ይውሰዱ፥ ሌላውንም ወይፈን ለኃጢአት መሥዋዕት ውሰድ። |
9. | ሌዋውያንንም በመገናኛው ድንኳን ፊት አቅርብ፤ የእስራኤልንም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስብ። |
10. | ሌዋውያንንም በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በሌዋውያን ላይ እጃቸውን ይጫኑባቸው። |
11. | አሮንም ሌዋውያን እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ከእስራኤል ልጆች መካከል ስጦታ አድርጎ፥ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። |
12. | ሌዋውያኑም በወይፈኖቹ ራሶች ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ፤ ለሌዋውያንም ስለ ማስተስረያ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርብ። |
13. | ሌዋውያንንም በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ስጦታ አድርገህ አቅርባቸው። |
14. | እንዲሁ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ። |
15. | ከዚያም በኋላ ሌዋውያን የመገናኛውን ድንኳን አገልግሎት ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ፤ ታነጻቸውማለህ፥ ስጦታም አድርገህ ታቀርባቸዋለህ። |
16. | እነርሱም ከእስራኤል ልጆች መካከል ፈጽሞ ለእኔ ተሰጥተዋልና፤ በእስራኤል ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ማኅፀን በሚከፍት ሁሉ ፋንታ ለእኔ ወስጄአቸዋለሁ። |
17. | በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ በገደልሁበት ቀን የእስራኤልን ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ሰው ወይም እንስሳ፥ ለእኔ ቀድሼአቸዋለሁና የእኔ ናቸው። |
18. | በእስራኤልም ልጆች በኵራት ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ወስጄአለሁ። |
19. | የእስራኤልም ልጆች ወደ መቅደሱ በቀረቡ ጊዜ መቅሠፍት እንዳያገኛቸው፥ ለእስራኤል ልጆች ያስተሰርዩላቸው ዘንድ፥ የእስራኤልንም ልጆች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለአሮንና ለልጆቹ ስጦታ አድርጌ ሰጥቼአቸዋለሁ። |
20. | ሙሴና አሮን የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲሁ በሌዋውያን ላይ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉላቸው። |
21. | ሌዋውያንም ከኃጢአት ተጣጠቡ፥ ልብሳቸውንም አጠቡ፤ አሮንም ስጦታ አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት አቀረባቸው፥ አሮንም ያነጻቸው ዘንድ አስተሰረየላቸው። |
22. | ከዚያም በኋላ ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በአሮንና በልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ይሠሩ ዘንድ ገቡ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረጉላቸው። |
23. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
24. | የሌዋውያን ሕግ ይህ ነው፤ ከሀያ አምስት ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት በመገናኛው ድንኳን ሥራ ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ። |
25. | ዕድሜአቸውም አምሳ ዓመት ሲሞላ የአገልግሎታቸውን ሥራ ይተዋሉ፥ ከዚያም በኋላ አይሠሩም፤ |
26. | የተሰጣቸውን ይጠብቁ ዘንድ ወንድሞቻቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለግላሉ፤ የድንኳኑን አገልግሎት አይሠሩም። እንዲሁ ስለ ሥራቸው በሌዋውያን ላይ ታደርጋለህ። |
← Numbers (8/36) → |