| ← Numbers (5/36) → |
| 1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 2. | የእስራኤል ልጆች ለምጻሙን ሁሉ፥ ፈሳሽ ነገርም ያለበትን ሁሉ፥ በሬሳም የረከሰውን ሁሉ ከሰፈሩ እንዲያወጡ እዘዛቸው፤ |
| 3. | ወንዱንና ሴቱን አውጡ፤ እኔ በመካከሉ የማድርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከሰፈሩ አውጡአቸው። |
| 4. | የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ ከሰፈሩ አወጡአቸው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው፥ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ። |
| 5. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 6. | ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። ወንድ ወይም ሴት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይተላለፍ ዘንድ ሰው የሚሠራውን ኃጢአት ቢሠራ፥ በዚያም ሰው ላይ በደል ቢሆን፥ በሠራው ኃጢአት ይናዘዝ፤ |
| 7. | የወሰደውንም በሙሉ ይመልስ አምስተኛውንም ይጨምርበት፥ ለበደለውም ሰው ይስጠው። |
| 8. | ነገር ግን ይመልስለት ዘንድ ሰውዮው ዘመድ ባይኖረው፥ ስለ በደል ለእግዚአብሔር የሚመልሰው ነገር ለካህኑ ይሁን፥ ይህም ስለ እርሱ ማስተሰረያ ከሚደረግበት አውራ በግ በላይ ይጨመር። |
| 9. | የእስራኤልም ልጆች ለካህኑ የሚያቀርቡት የተቀደሰ የማንሣት ቍርባን ሁሉ ለእርሱ ይሁን። |
| 10. | የተቀደሰ የሰው ነገር ሁሉ፥ ሰውም ለካህኑ የሚሰጠው ሁሉ ለእርሱ ይሁን። |
| 11. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 12. | ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። የማንኛውም ሰው ሚስት ከእርሱ ፈቀቅ ብትል፥ በእርሱም ላይ ብትበድል፥ |
| 13. | ከሌላም ሰው ጋር ብትተኛ፥ ከባልዋም ዓይን ቢሸሸግ፥ እርስዋም ተሰውራ ብትረክስ፥ ምስክርም ባይኖርባት፥ በምንዝርም ባትገኝ፥ |
| 14. | በባልዋም ላይ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ እርስዋም ስትረክስ ስለ ሚስቱ ቢቀና፤ ወይም እርስዋ ሳትረክስ የቅንዓት መንፈስ ቢመጣበት፥ ስለ ሚስቱም ቢቀና፤ |
| 15. | ያ ሰው ሚስቱን ወደ ካህኑ ያምጣት፥ የኢፍ መስፈሪያም አሥረኛ እጅ ገብስ ዱቄት ቍርባን ስለ እርስዋ ያምጣ፤ የቅንዓት ቍርባን ነውና፥ ኃጢአትንም የሚያሳስብ የመታሰቢያ ቍርባን ነውና ዘይት አያፍስስበት፥ ዕጣንም አይጨምርበት። |
| 16. | ካህኑም ያቀርባታል በእግዚአብሔርም ፊት ያቆማታል፤ |
| 17. | ካህኑም የተቀደሰ ውኃ በሸክላ ዕቃ ይወስዳል፤ ካህኑም በማደሪያው ውስጥ ካለው ትቢያ ወስዶ በውኃ ላይ ይረጨዋል፤ |
| 18. | ካህኑም ሴቲቱን በእግዚአብሔር ፊት ያቆማታል፥ የሴቲቱንም ራስ ይገልጣል፥ በእጅዋም ለመታሰቢያ የሚሆነውን የእህል ቍርባን፥ ለቅንዓት ቍርባን፥ ያኖራል፤ በካህኑም እጅ እርግማንን የሚያመጣው መራራ ውኃ ይሆናል። |
| 19. | ካህኑም ያምላታል፥ ሴቲቱንም እንዲህ ይላታል። ሌላ ወንድ አልተኛሽ፥ ባልሽንም አልተውሽ፥ ራስሽንም አላረከስሽ እንደ ሆነ፥ እርግማንን ከሚያመጣ ከዚህ መራራ ውኃ ንጹሕ ሁኚ፤ |
| 20. | ነገር ግን ባልሽን ትተሽ ረክሰሽ እንደ ሆነ፥ ከባልሽም ሌላ ከወንድ ጋር ተኝተሽ እንደሆነ፤ |
| 21. | ካህኑም ሴቲቱን በመርገም መሐላ ያምላታል፥ ካህኑም ሴቲቱን። እግዚአብሔር ጭንሽን እያሰለሰለ ሆድሽንም እየነፋ፥ እግዚአብሔር ለመርገምና ለመሐላ በሕዝብሽ መካከል ያድርግሽ፤ |
| 22. | እርግማንንም የሚያመጣ ይህ ውኃ ወደ ሆድሽ ይግባ፥ ሆድሽንም ይንፋው፥ ጭንሽንም ያበስብሰው ይላታል፤ ሴቲቱም። አሜን አሜን ትላለች። |
| 23. | ካህኑም እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ይጽፈዋል፥ በመራራውም ውኃ ይደመስሰዋል፤ |
| 24. | እርግማን የሚያመጣውንም መራራ ውኃ ለሴቲቱ ይጠጣታል፤ የእርግማኑም ውኃ በገባባት ጊዜ መራራ ይሆናል። |
| 25. | ካህኑም የቅንዓቱን የእህል ቍርባን ከሴቲቱ እጅ ይወስዳል፥ የእህሉንም ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዘዋል፥ ወደ መሠዊያውም ያመጣዋል፤ |
| 26. | ካህኑም ከእህሉ ቍርባን አንድ እፍኝ ሙሉ ለመታሰቢያው ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፥ ከዚያም በኋላ ለሴቲቱ ውኃውን ያጠጣታል። |
| 27. | ውኃውን ካጠጣት በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ ረክሳና በባልዋ ላይ አመንዝራ እንደ ሆነች፥ እርግማንን የሚያመጣው ውኃ ገብቶ መራራ ይሆንባታል፥ ሆድዋም ይነፋል፥ ጭንዋም ይሰለስላል፤ ሴቲቱም በሕዝብዋ መካከል ለመርገም ትሆናለች። |
| 28. | ያልረከሰች ያለ ነውርም እንደ ሆነች፥ ንጹሕ ትሆናለች፥ ልጆችንም ታረግዛለች። |
| 30. | ሴት ባልዋን ትታ በረከሰች ጊዜ፥ ወይም በሰው ላይ የቅንዓት መንፈስ በመጣበት ጊዜ፥ ስለ ሚስቱም በቀና ጊዜ፥ የቅንዓት ሕግ ይህ ነው፤ ሴቲቱንም በእግዚአብሔር ፊት ያቁማት፥ ካህኑም እንደዚህ ሕግ ሁሉ ያድርግባት። |
| 31. | ሰውዮውም ከኃጢአት ንጹሕ ይሆናል፥ ሴቲቱም ኃጢአትዋን ትሸከማለች። |
| ← Numbers (5/36) → |