| ← Numbers (4/36) → |
| 1. | እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። |
| 2. | ከሌዊ ልጆች መካከል በየወገናቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች የቀዓትን ልጆች ድምር ውሰድ፤ |
| 3. | ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ በመገናኛው ድንኳን ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡበትን ሁሉ ትደምራለህ። |
| 4. | በመገናኛው ድንኳን በንዋየ ቅድሳቱ ዘንድ የቀዓት ልጆች ሥራ ይህ ነው፤ |
| 5. | ከሰፈሩ በተነሡ ጊዜ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚሸፍነውን መጋረጃ ያውርዱ፥ የምስክሩንም ታቦት ይጠቅልሉበት፤ |
| 6. | በላዩም የአቆስጣውን ቁርበት መሸፈኛ ያድርጉበት፥ ከእርሱም በላይ ሁለንተናው ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። |
| 7. | በገጽ ኅብስት ገበታ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤ በእርሱም ላይ ወጭቶቹን፥ ጭልፋዎቹንም፥ ጽዋዎቹንም፥ ለማፍሰስም መቅጃዎቹን ያድርጉ፤ ሁልጊዜም የሚኖር እንጀራ በእርሱ ላይ ይሁን። |
| 8. | በእነርሱም ላይ ቀይ መጐናጸፊያ ይዘርጉ፥ በአቆስጣውም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። |
| 9. | ሰማያዊውንም መጐናጸፊያ ይውሰዱ፥ የሚያበራውንም መቅረዝ፥ ቀንዲሎቹንም፥ መኰስተሪያዎቹንም፥ የኩስታሪ ማድረጊያዎቹንም፥ እርሱንም ለማገልገል የዘይቱን ዕቃዎች ሁሉ ይሸፍኑ፤ |
| 10. | እርሱንና ዕቃዎቹን ሁሉ በአቆስጣ ቁርበት መሸፈኛ ውስጥ ያድርጉ፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት። |
| 11. | በወርቁም መሠዊያ ላይ ሰማያዊውን መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። |
| 12. | በመቅደስም ውስጥ የሚያገልግሉበትን የማገልገያውን ዕቃ ሁሉ ይውሰዱ፥ በሰማያዊውም መጐናጸፊያ ውስጥ ያስቀምጡት፥ በአቆስጣም ቁርበት መሸፈኛ ይሸፍኑት፥ በመሸከሚያውም ላይ ያድርጉት። |
| 13. | አመዱንም ከመሠዊያው ላይ ያስወግዱ፥ ሐምራዊውንም መጐናጸፊያ ይዘርጉበት፤ |
| 14. | የሚያገለግሉበትን ዕቃውን ሁሉም ማንደጃዎቹን ሜንጦቹንም መጫሪያዎቹንም ድስቶቹንም፥ የመሠዊያውን ዕቃ ሁሉ ያስቀምጡበት፤ በእርሱም የአቆስጣን ቁርበት መሸፈኛ ይዘርጉ፥ መሎጊያዎቹንም ያግቡ። |
| 15. | ከሰፈሩም ሲነሡ፥ አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና የመቅደሱን ዕቃ ሁሉ ከሸፈኑ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ የቀዓት ልጆች ሊሸከሙት ይመጣሉ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን አይንኩ። በመገናኛው ድንኳን ዘንድ የቀዓት ልጆች ሸክም ይህ ነው። |
| 16. | የካህኑም የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት በጣፋጩም ዕጣን ላይ፥ ሁልጊዜም በሚቀርበው በእህሉ ቍርባንና በቅባቱ ዘይት ላይ ይሾም፤ ማደሪያውን ሁሉ፥ በእርሱም ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ መቅደሱንና ዕቃውን ይጠብቃል። |
| 17. | እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። |
| 18. | የቀዓትን ወገኖች ነገድ ከሌዋውያን መካከል አታጥፉአቸው፤ |
| 19. | ነገር ግን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በቀረቡ ጊዜ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እንጂ እንዳይሞቱ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ አሮንና ልጆቹ ይግቡ፥ ለሰውም ሁሉ ሥራውንና ሸክሙን ይዘዙ፤ |
| 20. | ነገር ግን እንዳይሞቱ ንዋየ ቅድሳቱን ለድንገት እንኳ ለማየት አይግቡ። |
| 21. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 22. | የጌድሶንን ልጆች ድምር ደግሞ በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገኖቻቸውም ውሰድ። |
| 23. | የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ቍጠራቸው። |
| 24. | የጌድሶናውያን ወገኖች ሥራ በማገልገልና በመሸከም ይህ ነው፤ |
| 25. | የማደሪያውን መጋረጆች፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መደረቢያውን፥ በላዩም ያለውን የአቆስጣውን ቁርበት መደረቢያ፥ የመገናኛውንም ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥ |
| 26. | በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለውን የአደባባዩን መጋረጃ፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቻቸውንም፥ ለማገልገልም የሚሠሩበትን ዕቃ ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህ ያገልግሉ። |
| 27. | የጌድሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፥ ሸክማቸውም ሁሉ፥ ሥራቸውም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ ትእዛዝ ይሁን፤ የሚደርስባቸውንም ሸክም ሁሉ ትነግሩአቸዋላችሁ። |
| 28. | የጌድሶናውያን ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ይህ ነው፤ ከካህኑ ከአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች ይሆናሉ። |
| 29. | የሜራሪንም ልጆች በየወገናቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቍጠራቸው። |
| 30. | የመገናኛውን ድንኳን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የሚገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ቍጠራቸው። |
| 31. | በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ባለው አገልግሎታቸው ሁሉ፥ የማደሪያው ሳንቆች፥ መወርወሪያዎቹም፥ ተራዳዎቹም፥ እግሮቹም፥ |
| 32. | በዙሪያውም የሚቆሙት የአደባባዩ ምሰሶች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም፥ ዕቃዎቹና ማገልገያዎቹ ሸክማቸው ነው፤ የሚጠብቁትንም የሸክማቸውን ዕቃ ሁሉ በስማቸው ቍጠሩ። |
| 33. | የሜራሪ ልጆች ወገኖች አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ዘንድ ከካህኑ ክአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች በየአገልግሎታቸው ሁሉ ይህ ነው። |
| 34. | ሙሴና አሮንም የሕቡም አለቆች የቀዓትን ልጆች በየወገናቸው በየአባቶቻቸውም ቤቶች ቈጠሩአቸው። |
| 35. | በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ወደ አገግሎት የገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉትን ቈጠሩአቸው፤ |
| 36. | በየወገናቸውም ከእነርሱ የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ነበሩ። |
| 37. | እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከቀዓታውያን ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው። |
| 38. | በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት የጌድሶን ልጆች፥ |
| 39. | በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለአገልግሎት የገቡት፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥ |
| 40. | በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች የተቈጠሩት ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ ነበሩ። |
| 41. | እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለገሉት ሁሉ፥ ከጌድሶን ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው። |
| 42. | በየወገናቸውም በየአባቶቻቸውም ቤቶች ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ |
| 43. | በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ወደ አገልግሎት የገቡት ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥ |
| 44. | በየወገናቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። |
| 45. | እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ፥ ከሜራሪ ልጆች ወገኖች የተቈጠሩት፥ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ እነዚህ ናቸው። |
| 46. | በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች ከሌዋውያን የተቈጠሩት ሁሉ፥ ሙሴና አሮን የእስራኤልም አለቆች የቈጠሩአቸው፥ |
| 47. | በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራውን ለመሥራትና ዕቃውን ለመሸከም የገቡት ሁሉ፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ አምሳ ዓመት ድረስ ያሉት፥ |
| 48. | ከእነርሱ የተቈጠሩት ስምንት ሺህ እምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ። |
| 49. | እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ እያንዳንዳቸው በየአገልግሎታቸውና በየሸክማቸው በሙሴ እጅ ተቈጠሩ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በእርሱ ተቈጠሩ። |
| ← Numbers (4/36) → |