← Numbers (36/36) |
1. | ከዮሴፍ ልጆች ወገኖች የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጆች ወገን አለቆች ቀረቡ፥ በሙሴና በእስራኤልም ልጆች አባቶች አለቆች ፊት ተናገሩ፤ |
2. | አሉም። ምድሪቱን ለእስራኤል ልጆች ርስት አድርገህ በዕጣ ከፍለህ ትሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር አንተን ጌታችንን አዘዘህ፤ እግዚአብሔርም የወንድማችንን የሰለጰዓድን ርስት ለሴቶች ልጆቹ ትሰጥ ዘንድ አንተን ጌታችንን አዘዘ። |
3. | ከሌላም ከእስራኤል ልጆች ነገድ ባል ቢያገቡ፥ ርስታቸው ከአባቶቻችን ርስት ይነቀላል፥ እነርሱም ለሚሆኑበት ለሌላው ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እንደዚህም የርስታችን ዕጣ ይጐድላል። |
4. | ለእስራኤልም ልጆች ኢዮቤልዩ በመጣ ጊዜ ርስታቸው ለሚሆኑበት ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እንደዚህም ርስታቸው ከአባቶቻችን ነገድ ርስት ይጐድላል። |
5. | ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። የዮሴፍ ልጆች ነገድ በእውነት ተናገሩ። |
6. | እግዚአብሔር ስለ ሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ የወደዱትን ያግቡ፤ ነገር ግን ከአባታቸው ነገድ ብቻ ያግቡ። |
7. | እንደዚህም የእስራኤል ልጆች ርስት ከነገድ ወደ ነገድ ምንም አይተላለፍ፤ ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ወደ አባቶቹ ነገድ ርስት ይጠጋ። |
8. | ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ሰው የአባቶቹን ርስት ይወርስ ዘንድ፥ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ ርስት ያላት ሴት ልጅ ሁሉ ከአባትዋ ነገድ ባል ታግባ። |
9. | እንደዚህም ከአንድ ነገድ ወደ ሌላ ነገድ ምንም ርስት አይተላለፍ ከእስራኤልም ልጆች ነገድ እያንዳንዱ ወደ ርስቱ ይጠጋ። |
10. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች አደረጉ። |
11. | የሰለጰዓድ ልጆች ማህለህ፥ ቲርጻ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ኑዓ ከአባታቸው ወንድሞች ልጆች ጋር ተጋቡ። |
12. | ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ልጆች ወገኖች ባሎቻቸውን አገቡ፥ ርስታቸውም በአባታቸው ነገድ ጸና። |
13. | እግዚአብሔር በሙሴ እጅ የእስራኤልን ልጆች በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ ያዘዛቸው ትእዛዝና ፍርድ እነዚህ ናቸው። |
← Numbers (36/36) |