| ← Numbers (33/36) → |
| 1. | የእስራኤልም ልጆች ጕዞ ከሙሴና ከአሮን እጅ በታች በጭፍሮቻቸው ከግብፅ በወጡ ጊዜ እንዲህ ነበረ። |
| 2. | ሙሴም በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ጕዞአቸው አወጣጣቸውን ጻፈ፤ እንደ አወጣጣቸውም ጕዞአቸው እንዲህ ነበረ። |
| 3. | በመጀመሪያው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን ከራምሴ ተጓዙ፤ ከፋሲካ በኋላ በነጋው የእስራኤል ልጆች ግብፃውያን ሁሉ እያዩ ከፍ ባለች እጅ ወጡ። |
| 4. | በዚያም ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔር የገደላቸውን በኵሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ በአማልክቶቻቸውም ደግሞ እግዚአብሔር ፈረደባቸው። |
| 5. | የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተጕዘው በሱኮት ሰፈሩ። |
| 6. | ከሱኮትም ተጕዘው በምድረ በዳ ዳርቻ ባለች በኤታም ሰፈሩ። |
| 7. | ከኤታምም ተጕዘው በበኣልዛፎን ፊት ወደ ነበረች ወደ ፊሀሒሮት ተመለሱ፤ በሚግዶልም ፊት ለፊት ሰፈሩ። |
| 8. | ከፊሀሒሮትም ተጕዘው በባሕሩ ውስጥ ወደ ምድረ በዳ አለፉ፤ በኤታምም በረሀ የሦስት ቀን መንገድ ሄደው በማራ ሰፈሩ። |
| 9. | ከማራም ተጕዘው ወደ ኤሊም መጡ፤ በኤሊምም አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮች ሰባ ዘንባቦችም ነበሩ፤ በዚያም ሰፈሩ። |
| 10. | ከኤሊምም ተጕዘው በኤርትራ ባሕር ዳር ሰፈሩ። |
| 11. | ከኤርትራም ባሕር ተጕዘው በሲን ምድረ በዳ ሰፈሩ። |
| 12. | ከሲን ምድረ በዳም ተጕዘው በራፋቃ ሰፈሩ። |
| 13. | ከራፋቃም ተጕዘው በኤሉስ ሰፈሩ። |
| 14. | ከኤሉስም ተጕዘው በራፊዲም ሰፈሩ፤ በዚያም ሕዝቡ የሚጠጡት ውኃ አልነበረም። |
| 15. | ከራፊዲምም ተጕዘው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ። |
| 16. | ከሲናም ምድረ በዳ ተጕዘው በምኞት መቃብር ሰፈሩ። |
| 17. | ከምኞት መቃብርም ተጕዘው በሐጼሮት ሰፈሩ። |
| 18. | ከሐጼሮትም ተጕዘው በሪትማ ሰፈሩ። |
| 19. | ከሪትማም ተጕዘው በሬሞን ዘፋሬስ ሰፈሩ። |
| 20. | ከሬሞን ዘፋሬስም ተጕዘው በልብና ሰፈሩ። |
| 21. | ከልብናም ተጕዘው በሪሳ ሰፈሩ። |
| 22. | ከሪሳም ተጕዘው በቀሄላታ ሰፈሩ። |
| 23. | ከቀሄላታም ተጕዘው በሻፍር ተራራ ሰፈሩ። |
| 24. | ከሻፍር ተራራም ተጕዘው በሐራዳ ሰፈሩ። |
| 25. | ከሐራዳም ተጕዘው በመቅሄሎት ሰፈሩ። |
| 26. | ከመቅሄሎትም ተጕዘው በታሐት ሰፈሩ። |
| 27. | ከታሐትም ተጕዘው በታራ ሰፈሩ። |
| 28. | ከታራም ተጕዘው በሚትቃ ሰፈሩ። |
| 29. | ከሚትቃም ተጕዘው በሐሽሞና ሰፈሩ። |
| 30. | ከሐሽሞናም ተጕዘው በሞሴሮት ሰፈሩ። |
| 31. | ከሞሴሮትም ተጕዘው በብኔያዕቃን ሰፈሩ። |
| 32. | ከብኔያዕቃንም ተጕዘው በሖርሃጊድጋድ ሰፈሩ። |
| 33. | ከሖርሃጊድጋድም ተጕዘው በዮጥባታ ሰፈሩ። |
| 34. | ከዮጥባታም ተጕዘው በዔብሮና ሰፈሩ። |
| 35. | ከዔብሮናም ተጕዘው በዔጽዮንጋብር ሰፈሩ። |
| 36. | ከዔጽዮንጋብርም ተጕዘው በጺን ምድረ በዳ ሰፈሩ፤ ይህችም ቃዴስ ናት። |
| 37. | ከቃዴስም ተጕዘው በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ ሰፈሩ። |
| 38. | ካህኑም አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ሖር ተራራ ላይ ወጣ፥ በዚያም የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በአርባኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሞተ። |
| 39. | አሮንም በሖር ተራራ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሀያ ሦስት ዓመት ነበር። |
| 40. | በከነዓን ምድርም በደቡብ በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ የእስራኤል ልጆች እንደ መጡ ሰማ። |
| 41. | እነርሱም ከሖር ተራራ ተጕዘው በሴልሞና ሰፈሩ። |
| 42. | ከሴልሞናም ተጕዘው በፉኖን ሰፈሩ። |
| 43. | ከፉኖንም ተጕዘው በኦቦት ሰፈሩ። |
| 44. | ከኦቦትም ተጕዘው በሞዓብ ዳርቻ ባለው በጋይ ሰፈሩ። |
| 45. | ከጋይም ተጕዘው በዲቦንጋድ ሰፈሩ። |
| 46. | ከዲቦንጋድም ተጕዘው በዓልሞንዲብላታይም ሰፈሩ። |
| 47. | ከዓልሞንዲብላታይምም ተጕዘው በናባው ፊት ባሉ በዓብሪም ተራሮች ላይ ሰፈሩ። |
| 48. | ከዓብሪምም ተራሮች ተጕዘው በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ባለው በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፈሩ። |
| 49. | በዮርዳኖስም አጠገብ በሞዓብ ሜዳ ላይ ከቤትየሺሞት እስከ አቤልሰጢም ድረስ ሰፈሩ። |
| 50. | እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 51. | ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ |
| 52. | የአገሩን ሰዎች ሁሉ ከፊታችሁ ታሳድዳላችሁ፥ የተቀረጹትንም ድንጋዮቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፥ በኮረብታ ላይ ያሉትን መስገጃዎቻቸውንም ታፈርሳላችሁ፤ |
| 53. | ምድሪቱንም ለእናንተ ርስት አድርጌ ሰጥቼአችኋለሁና ምድሪቱን ትወርሱአታላችሁ ትቀመጡባታላችሁም። |
| 54. | ምድሪቱንም በየወገኖቻችሁ በዕጣ ትወርሳላችሁ፤ ለብዙዎች እንደ ብዛታቸው ለጥቂቶቹም እንደ ጥቂትነታቸው መጠን ርስትን ትሰጣላችሁ፤ እያዳንዱ ሁሉ ዕጣ እንደ ወደቀለት በዚያ ርስቱ ይሆናል፤ በየአባቶቻችሁ ነገዶች ትወርሳላችሁ። |
| 55. | የአገሩንም ሰዎች ከፊታችሁ ባታሳድዱ፥ ያስቀራችኋቸው ለዓይናችሁ እንደ እሾህ ለጎናችሁም እንደሚወጋ ነገር ይሆኑባችኋል፥ በምትቀመጡባትም ምድር ያስጨንቁአችኋል። |
| 56. | እኔም በእነርሱ አደርገው ዘንድ ያሰብሁትን በእናንተ አደርግባችኋለሁ። |
| ← Numbers (33/36) → |