← Numbers (31/36) → |
1. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
2. | ስለ እስራኤል ልጆች በቀል ምድያማውያንን ተበቀል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ወገኖችህ ትከማቻለህ። |
3. | ሙሴም ሕዝቡን። ከእናንተ መካከል ሰዎች ለጦርነት ይሰለፉ፤ ስለ እግዚአብሔር በቀል ምድያምን ይበቀሉ ዘንድ በምድያም ላይ ይሂዱ፤ |
4. | ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ከየነገዱ አንድ ሺህ ሰው ወደ ጦርነት ስደዱ ብሎ ተናገራቸው። |
5. | ከእስራኤልም አእላፋት አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ፥ ለጦርነት የተሰለፉ ሰዎች ተሰጡ። |
6. | ሙሴም ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ ወደ ጦርነት ሰደደ፤ እነርሱንና የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ወደ ጦርነት ሰደዳቸው፤ የመቅደሱንም ዕቃ የሚነፋውንም መለከት በእጁ ሰጠው። |
7. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ከምድያም ጋር ተዋጉ፥ ወንዶችንም ሁሉ ገደሉ። |
8. | ከተገደሉትም ጋር የምድያምን ነገሥታት ገደሉአቸው፤ አምስቱም የምድያም ነገሥታት ኤዊ፥ ሮቆም፥ ሱር፥ ሑር፥ ሪባ ነበሩ፤ የቢዖርንም ልጅ በለዓምን ደግሞ በሰይፍ ገደሉት። |
9. | የእስራኤልም ልጆች የምድያምን ሴቶችና ልጆቻቸውን ማረኩ፤ እንስሶቻቸውንና መንጎቻቸውንም ዕቃቸውንም ሁሉ በዘበዙ። |
10. | የተቀመጡባቸውን ከተሞቻቸውን ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። |
11. | የሰውንና የእንስሳን ምርኮና ብዝበዛ ሁሉ ወሰዱ። |
12. | የማረኩአቸውንም ሰዎች ምርኮውንና ብዝበዛውን ወደ ሙሴና ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር፥ በዮርዳኖስም አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ወዳለው ሰፈር አመጡ። |
13. | ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም የማኅበሩም አለቆች ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ ሊገናኙአቸው ወጡ። |
14. | ሙሴም ከዘመቻ በተመለሱት በጭፍራ አለቆች፥ በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ። |
15. | ሙሴም አላቸው። በውኑ ሴቶችን ሁሉ አዳናችኋቸውን? |
16. | እነሆ፥ እነዚህ በፌጎር ምክንያት በበለዓም ምክር እግዚአብሔርን ይበድሉ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ዕንቅፋት ሆኑ፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሠፍት ሆነ። |
17. | አሁን እንግዲህ ከልጆቹ ወንዱን ሁሉ ግደሉ፥ ወንድንም በመኝታ የሚያውቁትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ። |
18. | ወንድን የማያውቁትን ሴቶች ልጆችን ሁሉ ግን ለራሳችሁ አድኑአቸው። |
19. | ከሰፈሩም ውጭ ሰባት ቀን ስፈሩ፤ ሰውን የገደለ ሁሉ የተገደለውንም የዳሰሰ ሁሉ፥ እናንተ የማረካችኋቸውም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሰውነታችሁን ንጹሕ አድርጉ። |
20. | ልብስንም፥ ከቁርበትም የተዘጋጀውን ሁሉ፥ ከፍየልም ጠጕር ከእንጨትም የተሠራውን ሁሉ ንጹሕ አድርጉ። |
21. | ካህኑም አልዓዛር ከሰልፍ የመጡትን ሰዎች አላቸው። እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘው የሕጉ ሥርዓት ይህ ነው፤ |
22. | ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንም፥ ብረቱንም፥ ቆርቆሮውንም፥ |
23. | አረሩንም፥ በእሳት ለማለፍ የሚችለውን ሁሉ በእሳት ታሳልፉታላችሁ፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በማንጻት ውኃ ደግሞ ይጠራል። በእሳትም ለማለፍ የማይችለውን በውኃ ታሳልፉታላችሁ። |
24. | በሰባተኛውም ቀን ልብሳችሁን እጠቡ፥ ንጹሕም ትሆናላችሁ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ትቀርባላችሁ። |
25. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
26. | አንተና ካህኑ አልዓዛር የማኅበሩም አባቶች አለቆች የተማረኩትን ሰውና እንስሳ ቍጠሩ። |
27. | ምርኮውንም በተዋጉትና ወደ ሰፍል በወጡት፥ በማኅበሩም ሁሉ መካከል አስተካክለህ ክፈል። |
28. | ከእነዚያም ከተዋጉት ወደ ሰልፍም ከወጡት ሰልፈኞች ዘንድ፥ ከሰዎችም ከበሬዎችም ከአህዮችም ከመንጎችም ከአምስት መቶ አንድ ለእግዚአብሔር ግብር አውጣ። |
29. | ከድርሻቸው ወስደህ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን ለካህኑ ለአልዓዛር ስጠው። |
30. | ከእስራኤልም ልጆች ድርሻ ከሰዎች ከበሬዎችም ከአህዮችም ከመንጎችም ከከብቶችም ሁሉ ከአምሳ አንድ ትወስዳለህ፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ለሌዋውያን ትሰጣለህ። |
31. | ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። |
32. | ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎችም ከወሰዱት ብዝበዛ ያስቀሩት ምርኮ እንዲህ ሆነ፤ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺህ በጎች፥ |
34. | ሰባ ሁለት ሺህ በሬዎች፥ ስድሳ አንድ ሺህ አህዮች፥ |
35. | ወንድ ከማያውቁ ሴቶችም ሠላሳ ሁለት ሺህ ነፍስ። |
36. | በዘመቻም ለነበሩ ሰዎች ድርሻ የሆነ እኵሌታ ከበግ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች ነበረ፥ |
37. | ከበጎችም የእግዚአብሔር ግብር ስድስት መቶ ሰባ አምስት ነበረ። |
38. | በሬዎችም ሠላሳ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ሰባ ሁለት ነበረ። |
39. | አህዮቹም ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ስድሳ አንድ ነበረ። |
40. | ሰዎቹም አሥራ ስድስት ሺህ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ሠላሳ ሁለት ነበረ። |
41. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን የሆነውን ግብር ለካህኑ ለአልዓዛር ሰጠው። |
42. | ከእስራኤል ልጆች እኩሌታም፥ ወደ ሰልፍ ከወጡት ወንዶች ላይ ሙሴ የለየው፥ |
43. | የማኅበሩ ድርሻ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች፥ |
44. | ሠላሳ ስድስት ሺህ በሬዎች፥ |
45. | ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ አህዮች፥ |
46. | አሥራ ስድስት ሺህ ሰዎች ነበሩ። |
47. | ከእስራኤል ልጆች ድርሻ ሙሴ ከሰውና ከእንስሳ ከአምሳ አንድ ወሰደ፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የእግዚአብሔርን ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ሰጠ። |
48. | በሠራዊት አእላፋት ላይ የተሾሙት አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች፥ ወደ ሙሴ ቀረቡ፥ |
49. | ሙሴንም። እኛ ባሪያዎችህ ወደ ሰልፍ የወጡትን ከእጃችን በታች ያሉትን ቈጠርን፥ ከእኛም አንድ አልጐደለም። |
50. | ሰውም ሁሉ ካገኘው ከወርቅ ዕቃ፥ ከእግር አልቦም፥ ከአምባርም፥ ከቀለበትም፥ ከጕትቻም፥ ከድሪውም ለነፍሳችን በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይልን ዘንድ ለእግዚአብሔር መባ አምጥተናል አሉት። |
51. | ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁንና በልዩ ልዩ የተሠራውን ዕቃ ሁሉ ከእጃቸው ተቀበሉ። |
52. | ሻለቆችም የመቶ አለቆችም ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን ያቀረቡት ወርቅ ሁሉ አሥራ ስድስት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ሰቅል ነበረ። |
53. | ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ሁሉ ከምርኮአቸው ለራሳቸው ወሰዱ። |
54. | ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁን ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ወስደው በእግዚአብሔር ፊት ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ወደ መገናኛው ድንኳን አገቡት። |
← Numbers (31/36) → |