| ← Numbers (3/36) → |
| 1. | እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ሙሴን በተናገረበት ቀን የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበረ። |
| 2. | የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው፤ በኵሩ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር። |
| 3. | የተቀቡ ካህናት በክህነትም ያገለግሉ ዘንድ የቀደሳቸው የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው። |
| 4. | ናዳብና አብዩድ በሲና ምድረ በዳ በእግዚአብሔር ፊት ልዩ እሳት ባቀረቡ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፤ ልጆችም አልነበሩአቸውም። አልዓዛርና ኢታምር በአባታቸው በአሮን ፊት በክህነት ያገለግሉ ነበር። |
| 5. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 6. | የሌዊን ነገድ አቅርበህ ያገለግሉት ዘንድ በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው። |
| 7. | የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ እርሱንና ማኅበሩን ሁሉ ለማገልገል የሚያስፈልገውን ነገር በመገናኛው ድንኳን ፊት ይጠብቁ። |
| 8. | የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ የመገናኛውን ድንኳን ዕቃ ሁሉ ይጠብቁ፥ የእስራኤልን ልጆች ለማገልገል የሚያስፈልገውንም ነገር ይጠብቁ። |
| 9. | ሌዋውያንንም ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣለህ፤ ከእስራኤል ልጆች ለእርሱ ፈጽመው ተሰጡ። |
| 10. | አሮንንና ልጆቹን አቁማቸው፥ ክህነታቸውንም ይጠብቁ፤ ሌላ ሰውም ቢቀርብ ይገደል። |
| 11. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 12. | እነሆ፥ እኔ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ማኅፀን በሚከፍተው በበኵሩ ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤ |
| 13. | በኵር ሁሉ ለእኔ ነውና ሌዋውያን ለእኔ ይሁኑ፤ በግብፅ ምድር በኵርን ሁሉ በመታሁ ቀን፥ ከእስራኤል ዘንድ በኵርን ሁሉ፥ ሰውንና እንስሳን፥ ለእኔ ለይቼአለሁ፤ ለእኔ ይሁኑ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ። |
| 14. | እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 15. | የሌዊን ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገናቸውም ቍጠር፤ ወንዱን ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን ቍጠራቸው። |
| 16. | ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዳዘዘው ቈጠራቸው። |
| 17. | የሌዊ ልጆች በየስማቸው እነዚህ ናቸው፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ። |
| 18. | የጌድሶንም ልጆች ስሞች በየወገናቸው እነዚህ ናቸው፤ ሎቤኒ፥ ሰሜኢ። |
| 19. | የቀዓትም ልጆች በየወገናቸው እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል። |
| 20. | የሜራሪም ልጆች በየወገናቸው፤ ሞሖሊ፥ ሙሲ። የሌዋውያን ወገኖች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ናቸው። |
| 21. | ለጌድሶን የሎቤናውያን ወገን የሰሜአውያንም ወገን ነበሩት፤ የጌድሶናውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው። |
| 22. | ከእነርሱ የተቈጠሩት የወንዶች ሁሉ ቍጥር ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። |
| 23. | የጌድሶናውያን ወገኖች ከማደሪያው በኋላ በምዕራብ ብኩል ይሰፍራሉ። |
| 24. | የጌድሶናውያንም አባቶች ቤት አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል። |
| 25. | ጌድሶናውያንም በመገናኛው ድንኳን የሚጠብቁት ማደሪያው፥ ድንኳኑም፥ መደረቢያውም፥ የመገናኛው ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥ |
| 26. | በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለው የአደባባዩ መጋረጆች፥ የአደባባዩም ደጃፍ መጋረጃ፥ ለማገልገሉም ያሉት ገመዶች ሁሉ ይሆናል። |
| 27. | ከቀዓትም የእንበረማውያን ወገን፥ የይስዓራውያንም ወገን፥ የኬብሮናውያንም ወገን፥ የዑዝኤላውያንም ወገን ነበሩ፤ የቀዓታውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው። |
| 28. | ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ፤ መቅደሱንም ይጠብቁ ነበር። |
| 29. | የቀዓት ልጆች ወገኖች በማደሪያው አጠገብ በደቡብ በኩል ይሰፍራሉ። |
| 30. | የቀዓታውያንም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የዑዝኤል ልጅ ኤሊሳፈን ይሆናል። |
| 31. | ታቦቱንም፥ ገበታውንም፥ መቅረዙንም፥ መሠዊያዎቹንም፥ የሚያገለግሉበትንም የመቅደሱን ዕቃ፥ መጋረጃውንም፥ ማገልገያውንም ሁሉ ይጠብቃሉ። |
| 32. | የሌዋውያንም አለቆች አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ይሆናል፤ እርሱም መቅደሱን በሚጠብቁት ላይ ይሆናል። |
| 33. | ከሜራሪ የሞሖላውያን ወገን የሙሳያውያንም ወገን ነበሩ፤ የሜራሪ ወገኖች እነዚህ ናቸው። |
| 34. | ከእነርሱም ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። |
| 35. | የሜራሪም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ነበረ፤ በማደሪያው አጠገብ በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ። |
| 36. | የሜራሪም ልጆች የሚጠብቁት የማደሪያው ሳንቆች፥ መወርወሪያዎችም፥ ተራዳዎችም፥ እግሮቹም፥ ዕቃውም ሁሉ፥ |
| 37. | ማገልገያውም ሁሉ፥ በዙሪያውም የሚቆሙ የአደባባይ ምሰሶች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም ይሆናሉ። |
| 38. | በማደሪያውም ፊት በምሥራቅ በኩል በመገናኛው ድንኳን ፊት በስተ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት ሙሴና አሮን ልጆቹም ይሆናሉ፥ መቅደሱንም ለእስራኤል ልጆች ይጠብቃሉ፤ ልዩም ሰው ቢቀርብ ይገደል። |
| 39. | በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ ከሌዋውያን ወንዶች ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ በየወገናቸው የተቈጠሩት ሁሉ ሀያ ሁለት ሺህ ነበሩ። |
| 40. | እግዚአብሔርም ሙሴን። የእስራኤልን ልጆች ወንዱን በኵር ሁሉ ቍጠር፤ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን የስማቸውን ቍጥር ውሰድ፤ |
| 41. | ሌዋውያንንም በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእስራኤል ልጆች እንስሶች በኵር ሁሉ ፋንታ ለእኔ ለእግዚአብሔር ውሰድ አለው። |
| 42. | ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኵር ሁሉ ቈጠረ። |
| 43. | ከእነርሱም የተቈጠሩ ወንዶች በኵሮች ሁሉ የበስማቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበሩ። |
| 44. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
| 45. | ሌዋውያንን በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእንስሶቻቸው ፋንታ ውሰድ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። |
| 46. | በሌዋውያን ላይ ከእስራኤል ልጆች በኵር ስለ ተረፉት ስለ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ቤዛ፥ በየራሱ አምስት ሰቅል ውሰድ፤ |
| 47. | እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ትወስዳለህ፤ ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ነው። |
| 48. | ስለ ተረፉትም የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ። |
| 49. | ሙሴም በሌዋውያን ከተቤዡት በላይ ከተረፉት ዘንድ የመቤዣውን ገንዘብ ወሰደ። |
| 50. | ከእስራኤል ልጆች በኵሮች ገንዘቡን ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ወሰደ። |
| 51. | እንደ እግዚአብሔርም ቃል፥ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው፥ ሙሴ የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ። |
| ← Numbers (3/36) → |