| ← Numbers (24/36) → |
| 1. | በለዓምም እግዚአብሔር እስራኤልን ይባርክ ዘንድ እንዲወድድ ባየ ጊዜ፥ አስቀድሞ ያደርግ የነበረውን አስማት ይሻ ዘንድ አልሄደም፤ ነገር ግን ወደ ምድረ በዳ ፊቱን አቀና። |
| 2. | በለዓምም ዓይኑን አንሥቶ እስራኤል በየነገዱ ተቀምጦ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ መጣ። |
| 3. | ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዓይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤ |
| 4. | የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል። |
| 5. | ያዕቆብ ሆይ፥ ድንኳኖችህ፥ እስራኤል ሆይ ማደሪያዎችህ ምንኛ ያምራሉ! |
| 6. | እንደ ሸለቆች፥ በወንዝ ዳር እንዳሉ አትክልቶች፥ እግዚአብሔር እንደ ተከለው እሬት በውኃም ዳር እንዳሉ ዝግባዎች ተዘርግተዋል። |
| 7. | ከማድጋዎቹ ውኃ ይፈስሳል፥ ዘሩም በብዙ ውኆች ይሆናል፥ ንጉሡም ከአጋግ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፥ መንግሥቱም ይከበራል። |
| 8. | እግዚአብሔርም ከግብፅ አውጥቶታል፤ ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው፤ ጠላቶቹን አሕዛብን ይበላል፥ አጥንቶቻቸውንም ይሰባብራል፥ በፍላጾቹም ይወጋቸዋል። |
| 9. | እንደ አንበሳ ዐርፎ ተኝቶአል፥ እንደ እንስቲቱም አንበሳ ተጋድሞአል፤ ማን ያስነሣዋል? የሚመርቅህ ሁሉ የተመረቀ ይሁን፥ የሚረግምህም ሁሉ የተገመ ይሁን። |
| 10. | የባላቅም ቍጣ በበለዓም ላይ ነደደ፤ እጆቹንም አጨበጨበ፤ ባላቅም በለዓምን። ጠላቶቼን ትረግም ዘንድ ጠራሁህ፥ እነሆም፥ ሦስት ጊዜ ፈጽመህ መረቅሃቸው፤ አሁንም እንግዲህ ወደ ስፍራህ ሽሽ፤ |
| 11. | እኔ አከብርህ ዘንድ ወድጄ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን፥ እነሆ፥ ክብርህን ከለከለ አለው። |
| 13. | በለዓምም ባላቅን አለው። ባላቅ በቤቱ የሞላውን ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ፥ መልካሙን ወይም ክፉውን ከልቤ ለማድረግ የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ እግዚአብሔር የተናገረውን እርሱን እናገራለሁ ብዬ ወደ እኔ ለላክሃቸው መልእክተኞች አልተናገርኋቸውምን? |
| 14. | አሁንም፥ እነሆ፥ ወደ ሕዝቤ እሄዳለሁ፤ ና፥ ይህ ሕዝብ በኋለኛው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ። |
| 15. | ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤ |
| 16. | የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል። |
| 17. | አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤል በትር ይነሣል፥ የሞዓብንም ማዕዘኖች ይመታል፥ የሤትንም ልጆች ያጠፋል። |
| 18. | ኤዶምያስም ርስቱ ይሆናል፥ ጠላቱ ሴይር ደግሞ ርስቱ ይሆናል፤ እስራኤልም በኃይል ያደርጋል። |
| 19. | ከያዕቆብም የሚወጣ ገዥ ይሆናል፥ ከከተማውም የቀሩትን ያጠፋል። |
| 20. | አማሌቅንም አይቶ ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። አማሌቅ የአሕዛብ አለቃ ነበረ፤ ፍጻሜው ግን ወደ ጥፋት ይመጣል። |
| 21. | ቄናውያንንም አይቶ ምሳሌውን ይምስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ማደሪያህ የጸና ነው፥ ጎጆህም በአምባ ላይ ተሠርቶአል፤ |
| 22. | ነገር ግን አሦር እስኪማርክህ ድረስ ቄናዊው ለጥፋት ይሆናል። |
| 23. | ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። እግዚአብሔር ይህን ሲያደርግ አወይ! ማን በሕይወት ይኖራል? |
| 24. | ከኪቲም ዳርቻ መርከቦች ይመጣሉ፥ አሦርንም ያስጨንቃሉ፥ ዔቦርንም ያስጨንቃሉ፤ እርሱም ደግሞ ወደ ጥፋት ይመጣል። |
| 25. | በለዓምም ተነሣ፥ ተመልሶም ወደ ስፍራው ሄደ፤ ባላቅም ደግሞ መንገዱን ሄደ። |
| ← Numbers (24/36) → |