← Numbers (21/36) → |
1. | በደቡብም በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ በአታሪም መንገድ እስራኤል እንደ መጡ ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ሰልፍ አደረገ ከእነርሱም ምርኮ ማረከ። |
2. | እስራኤልም ለእግዚአብሔር። እነዚህን አሳልፈህ በእጄ ብትሰጣቸው ከተሞቻቸውን እርም ብዬ አጠፋለሁ ብሎ ስእለት ተሳለ። |
3. | እግዚአብሔርም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፥ ከነዓናውያንንም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱንም ከተሞቻቸውንም እርም ብለው አጠፉ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ሔርማ ብለው ጠሩት። |
4. | ከሖርም ተራራ ከኤዶምያስ ምድር ርቀው ሊዞሩ በኤርትራ ባሕር መንገድ ተጓዙ፤ የሕዝቡም ሰውነት ከመንገዱ የተነሣ ደከመ። |
5. | ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ። በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ። |
6. | እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ እባቦችን ሰደደ፥ ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ። |
7. | ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው። በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን በድለናል፤ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን አሉት። |
8. | ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። እግዚአብሔርም ሙሴን። እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል፤ የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው። |
9. | ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ። |
10. | የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኦቦትም ሰፈሩ። |
11. | ከኦቦትም ተጕዘው በሞዓብ ፊት ለፊት ባለችው ምድረ በዳ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል፥ በዒዬዓባሪም ሰፈሩ። |
12. | ከዚያም ተጕዘው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ። |
13. | ከዚያም ተጕዘው ከአሞራውያን ዳርቻ በሚወጣው ምድረ በዳ ውስጥ በአሮኖን ማዶ ሰፈሩ፤ አሮኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል ያለ የሞዓብ ዳርቻ ነውና። |
14. | ስለዚህ በእግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተባለ። ዋሄብ በሱፋ፥ የአርኖንም ሸለቆች፥ |
15. | ወደ ዔር ማደሪያ የሚወርድ በሞዓብም ዳርቻ የሚጠጋ የሸለቆች ፈሳሽ። |
16. | ከዚያም ወደ ብኤር ተጓዙ፤ ይኸውም እግዚአብሔር ሙሴን። ሕዝቡን ሰብስብ ውኃንም እሰጣቸዋለሁ ብሎ የተናገረለት ጕድጓድ ነው። |
17. | በዚያም ጊዜ እስራኤል ይህን መዝሙር ዘመረ። አንተ ምንጭ ሆይ፥ ፍለቅ፤ እናንተ ዘምሩለት፤ |
18. | በበትረ መንግሥት በበትራቸውም የሕዝብ አዛውንቶች ያጐደጐዱት፥ አለቆችም የቈፈሩት ጕድጓድ። |
19. | ከምድረ በዳም ወደ መቴና ተጓዙ፤ ከመቴናም ወደ ነሃሊኤል፥ ከነሃሊኤልም ወደ ባሞት፥ |
20. | ከባሞትም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ በሞዓብ በረሀ ወዳለው ሸለቆ ተጓዙ። |
22. | እስራኤልም። በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻና ወደ ወይን ቦታ አንገባም፤ ከጕድጓድም ውኃን አንጠጣም፤ ከምድርህ ዳርቻ እስክንወጣ ድረስ በንጉሥ ጐዳና እንሄዳለን ብለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞችን ላኩ። |
23. | ሴዎንም እስራኤል በምድሩ ላይ ያልፍ ዘንድ እንቢ አለ፤ ሴዎንም ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ እስራኤልንም ለመውጋት ወደ ምድረ በዳ ወጣ፥ ወደ ያሀጽም መጣ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ። |
24. | እስራኤልም በሰይፍ መታው፥ ምድሩንም ከአርኖን ጀምሮ እስከ አሞን ልጆች እስከ ያቦቅ ድረስ ወረሰ፤ የአሞንም ልጆች ዳርቻ የጸና ነበረ። |
25. | እስራኤልም እነዚህን ከተሞች ሁሉ ወሰደ፤ እስራኤልም በአሞራውያን ከተሞች ሁሉ በሐሴቦንና በመንደሮቹ ሁሉ ተቀመጠ። |
26. | ሐሴቦንም የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተማ ነበረ፤ እርሱም የፊተኛውን የሞዓብን ንጉሥ ወግቶ እስከ አርኖን ድረስ ምድሩን ሁሉ ከእጁ ወስዶ ነበር። |
27. | ስለዚህ በምሳሌ እንዲህ ተብሎ ተነገረ። ወደ ሐሴቦን ኑ፤ የሴዎን ከተማ ይሠራ፥ ይመሥረት፤ |
28. | እሳት ከሐሴቦን፥ ነበልባልም ከሴዎን ከተማ ወጣ፤ የሞዓብን ዔር፥ የአርኖንን ተራራ አለቆች በላ፤ |
29. | ሞዓብ ሆይ፥ ወዮልህ! የከሞስ ሕዝብ ሆይ፥ ጠፋህ፤ ወንዶች ልጆቹን ለሽሽት፥ ሴቶች ልጆቹንም ለምርኮ፥ ለአሞራውያን ንጉሥ ለሴዎን ሰጠ። |
30. | ገተርናቸው፤ ከሐሴቦን እስከ ዴቦን ድረስ ጠፉ፤ ኖፋም እስኪደርሱ እስከ ሜድባ አፈረስናቸው። |
31. | እስራኤልም እንደዚህ በአሞራውያን ምድር ተቀመጡ። |
32. | ሙሴም ሰላዮችን ወደ ኢያዜር ሰደደ፤ መንደሮችዋንም ወሰዱ፥ በዚያም የነበሩትን አሞራውያን አባረሩ። |
33. | ተመልሰውም በበሳን መንገድ ወጡ፤ የባሳንም ንጉሥ ዐግ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በኤድራይ ይወጋቸው ዘንድ ወጣ። |
34. | እግዚአብሔርም ሙሴን። እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሪቱንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦንም በተቀመጠው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግህ እንዲሁ ታደርግበታለህ አለው። |
35. | እርሱንና ልጆቹን ሕዝቡንም ሁሉ መቱ ሰውም አልቀረለትም፤ ምድሩንም ወረሱ። |
← Numbers (21/36) → |