← Numbers (20/36) → |
1. | የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በመጀመሪያው ወር ወደ ጺን ምድረ በዳ መጡ፤ ሕዝቡም በቃዴስ ተቀመጡ፤ ማርያምም በዚያ ሞተች፥ በዚያም ተቀበረች። |
2. | ለማኅበሩም ውኃ አልነበረም፤ በሙሴና በአሮንም ላይ ተሰበሰቡ። |
3. | ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት፥ እንዲህም ብለው ተናገሩት። ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር ፊት በሞቱ ጊዜ እኛም ምነው በሞትን ኖሮ! |
4. | እኛ ከብቶቻችንም በዚያ እንሞት ዘንድ የእግዚአብሔርን ጉባኤ ወደዚህ ምድረ በዳ ለምን አመጣችሁ? |
5. | ወደዚህ ክፉ ስፍራ ታመጡን ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? ዘርና በለስ ወይንም ሮማንም የሌለበት ስፍራ ነው፤ የሚጠጣም ውኃ የለበትም። |
6. | ሙሴና አሮንም ከጉባኤው ፊት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሂደው በግምባራቸው ወደቁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠላቸው። |
7. | እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። |
8. | በትርህን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን ሰብስቡ፥ ድንጋዩም ውኃን እንዲሰጥ እነርሱ ሲያዩ ተናገሩት፤ ከድንጋዩም ውኃ ታወጣላቸዋለህ፤ እንዲሁም ማኅበሩን ከብቶቻቸውንም ታጠጣላቸዋለህ። |
9. | ሙሴም እንደ ታዘዘ በትሩን ከእግዚአብሔር ፊት ወሰደ። |
10. | ሙሴና አሮንም ጉባኤውን በድንጋዩ ፊት ሰብስበው። እናንተ ዓመፀኞች፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ ከዚህ ድንጋይ ውኃን እናወጣላችኋለን? አላቸው። |
11. | ሙሴም እጁን ዘርግቶ ድንጋዩን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታው፤ ብዙም ውኃ ወጣ፥ ማኅበሩም ከብቶቻቸውም ጠጡ። |
12. | እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን። በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይህን ጉባኤ ይዛችሁ አትገቡም አላቸው። |
13. | የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ላይ ጠብ ያደረጉበት፥ እርሱም ቅዱስ መሆኑን የገለጠበት ይህ የመሪባ ውኃ ነው። |
14. | ሙሴም ከቃዴስ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ መልእክተኞችን እንዲህ ብሎ ላከ። ወንድምህ እስራኤል እንዲህ ይላል። ያገኘንን መከራ ሁሉ አንተ ታውቃለህ፤ |
15. | አባቶቻችን ወደ ግብፅ ወረዱ፥ በግብፅም እጅግ ዘመን ተቀመጥን ግብፃውያንም እኛንና አባቶቻችንን በደሉ፤ |
16. | ወደ እግዚአብሔርም በጮኽን ጊዜ ድምፃችንን ሰማ፥ መልአክንም ሰድዶ ከግብፅ አወጣን፤ እነሆም፥ በምድርህ ዳርቻ ባለችው ከተማ በቃዴስ ተቀምጠናል። |
17. | እባክህ፥ በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻም ወደ ወይንም አንገባም፥ ከጕድጓዶችም ውኃን አንጠጣም፤ በንጉሡ ጐዳና እንሄዳለን፥ ዳርቻህንም እስክናልፍ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም። |
18. | ኤዶምያስም። በሰይፍ እንዳልገጥምህ በምድሬ ላይ አታልፍም አለው። |
19. | የእስራኤልም ልጆች። በጐዳናው እንሄዳለን፥ እኔም ከብቶቼም ከውኃህ ብንጠጣ ዋጋውን እንከፍላለን፥ ሌላም ምንም አናደርግም፤ ብቻ በእግራችን እንለፍ አሉት። |
20. | እርሱም። አታልፍም አለ። ኤዶምያስም በብዙ ሕዝብና በጽኑ እጅ ሊገጥመው ወጣ። |
21. | ኤዶምያስም እስራኤል በዳርቻው እንዳያልፍ ከለከለ፤ ስለዚህ እስራኤል ከእርሱ ተመለሰ። |
22. | ከቃዴስም ተጓዙ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ወደ ሖር ተራራ መጡ። |
23. | እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። |
24. | አሮን ወደ ወገኑ ይከማች፤ በመሪባ ውኃ ዘንድ በቃሌ ላይ ስለ ዐመፃችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደ ሰጠኋት ምድር አይገባም። |
25. | አሮንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ ወደ ሖር ተራራ ላይ አምጣቸው፤ |
26. | ከአሮንም ልብሱን አውጣ፥ ልጁንም አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም ወደ ወገኑ ይከማች፥ በዚያም ይሙት። |
27. | ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘ አደረገ፤ ማኅበሩም ሁሉ እያዩ ወደ ሖር ተራራ ወጡ። |
28. | ሙሴም የአሮንን ልብስ አወጣ፥ ልጁንም አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም በዚያ በተራራው ራስ ላይ ሞተ፤ ሙሴና አልዓዛርም ከተራራው ወረዱ። |
29. | ማኅበሩም ሁሉ አሮን እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ፥ የእስራኤል ቤት ሁሉ ለአሮን ሠላሳ ቀን አለቀሱ። |
← Numbers (20/36) → |